የኢትዮጵያ ብሪክስን መቀላቀል ከዓለም አገራት ጋር የጋራ ልማትን ለማረጋገጥ እና ብሔራዊ ጥቅምን ለማስጠበቅ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ብሪክስን መቀላቀል ከዓለም አገራት ጋር የጋራ ልማትን ለማረጋገጥ እና ብሔራዊ ጥቅምን ለማስጠበቅ ነው
አዲስ አበባ ፤ ህዳር 20/2016 (ኢዜአ) ፦የኢትዮጵያ ብሪክስን መቀላቀል ከዓለም አገራት ጋር የጋራ ልማትን ለማረጋገጥ እና ብሔራዊ ጥቅምን ለማስጠበቅ መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ ገለጹ።
የውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት ከሲቪክ ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ጋር በመተባበር ኢትዮጵያን ወደ ብሪክስ መቀላቀሏ በሚኖረው ፋይዳ ላይ ከተለያዩ የሲቪል ድርጅት ተወካዮች ጋር በአዲስ አበባ የምክክር መድረክ እያካሄደ ነው።
በመድረኩ ላይ የተገኙት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ፤ የኢትዮጵያ ብሪክስን መቀላቀል ብሔራዊ ጥቅምን ማዕከል ያደረገ ስለመሆኑ አብራርተዋል።
የብሪክስ አባል መሆን በንግድ፣ በኢንቨስትመንት፣ በአማራጭ የልማት ፋይናንስ ምንጭ ማስፋት እና አጋርነትን ለማጎልበት የሚረዳ መሆኑንም አንስተዋል።
ብሪክስ የሁሉም አመለካከት ማዕከልና በዓለም ትልቅ ምጣኔ ሀብታዊ ጉልበት ያለው ስብስብ መሆኑንም አስረድተዋል።
ኢትዮጵያ በዓለም መድረክ ድምጿን ለማሰማት ተጨማሪ ዕድል የሚሰጥ በመሆኑ ትልቅ ዲፕሎሚሲ ስኬት መሆኑን ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ ብሪክስን የተቀላቀለችው ከየትኛውም ርዕዮተ ዓለም ጎራ ለመወገን ሳይሆን ከሁሉም የዓለም አገራት ጋር የጋራ ልማትን ለማረጋገጥ እና ብሔራዊ ጥቅምን ለማስጠበቅ መሆኑንም አምባሳደር ምስጋኑ ገልጸዋል።
በኢትዮጵያ የገፅታ ግንባታ እና የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ዕውቅና እንዲያገኝ በማድረግ ረገድ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች የላቀ ሚና እንዳላቸው ጠቅሰው የተዘጋጀው መድረክም ዋነኛ ዓላማ በብሪክስ ዙሪያ ሰፊ ግንዛቤ እንዲኖራቸው ለማስቻል ነው ብለዋል።
የሲቪክ ማህበረሰብ ድርጅት ባለስልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር ፋሲካው ሞላ፤ የሲቪክ ማህበረሰብ ድርጅቶች የውጭ ጉዳይን ጨምሮ በተለያዩ ጉዳዮች ለሀገር አስተዋጽኦ እያበረከቱ መሆኑን ጠቅሰዋል።
በብሪክስ አባልነት ጉዳይ ግንዛቤ መፈጠሩም ማህበራቱ የበኩላቸውን ሚና በላቀ መልኩ እንዲወጡ የሚያስችል መሆኑን ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ የብሪክስ አባልነት ጥያቄ በይፋ ተቀባይነት ያገኘው ባሳለፍነው ወርኃ ነሀሴ በደቡብ አፍሪካ በተካሄደው የብሪክስ አባል ሀገራት 15ኛ ጉባኤ መሆኑ ይታወቃል።
ኢትዮጵያን ጨምሮ ቡድኑን አዲስ የተቀላቀሉ አገራት ከመጪው የፈረንጆች አዲስ ዓመት መባቻ ጀምሮ የብሪክስ ሙሉ አባልነትን የሚያረጋግጡ ይሆናል።