ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ በ91ኛው ዓለም አቀፉ የፖሊስ ድርጅት ዓመታዊ ጠቅላላ ጉባኤ ላይ እየተሳተፈች ነው

አዲስ አበባ ፤ ህዳር 20/2016 (ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ በኦስትሪያ ዋና ከተማ ቪየና እየተካሄደ ባለዉ 91ኛው ዓለም አቀፉ የፖሊስ ድርጅት (INTERPOL) ዓመታዊ ጠቅላላ ጉባኤና የድርጅቱ 100ኛ ዓመት ክብረ በዓል ላይ እየተሳተፈች ትገኛለች።

የኢትዮጵያ ብሄራዊ ኢንተርፖልና ዓለም አቀፍ የፖሊስ ትብብር መምሪያ ኃላፊ ረዳት ኮሚሽነር ደጀኔ በቀለ በሰጡት መግለጫ፤ በኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገ/ሚካኤል የተመራው ልዑክ ከህዳር 17-21 ቀን 2016 ዓ.ም እየተካሄደ ባለው የድርጅቱ ጠቅላላ ጉባኤ እና የምስረታ ክብረ በዓል ላይ እየተሳተፈ መሆኑን ገልፀዋል።

በጉባኤው የድርጅቱ አባል ሀገራት ፖሊስ አዛዦች፣ ፖሊስ ተጠሪ የሆኑላቸው ሚኒስትሮች እና የተለያዩ ከፖሊስ ጋር በአጋርነት የሚሰሩ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች እየተሳተፉ እንደሚገኙ ተገልጿል፡፡

ልዑካን ቡድኑ የኦስትሪያ ፖሊስ ስለሚያከናውናቸው የወንጀል መከላከልና ምርመራ ሥራ እንዲሁም የተጠርጣሪ አያያዝና ፖሊስ ስለሚጠቀምባቸው ትጥቆች፣ አልባሳት እና ተሽከርካሪዎች ገለጻ አንደተደረገለት በመግለጫው ተጠቁሟል፡፡

ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገብረሚካኤል ስለ ኢትዮጵያ ፖሊስ አሠራር፣ በሪፎርሙ እየተከናወነ ስላለው ተግባር፣ ተቋሙ እየተጠቀመባቸው ስላለዉ ዘመናዊ የቴክኖሎጂ መሣሪያዎችና የአሠራር ልምዳቸውን እንዳካፈሉም ተገልጿል።

መግለጫው አያይዞ ከጉባኤው ጎን ለጎን ልዑካን ቡድኑ ከተለያዩ ሀገራትና ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ጋር ውይይትና የልምድ ልውውጥ ማድረጉን አመላክቷል። 

ኢትዮጵያ ከድርጅቱ አባል ሀገራት ጋር ያላትን የፖሊስ ለፖሊስ ግንኙነት የበለጠ ለማጠናከርና ተባብራ ለመስራት እንዲሁም ድንበር ተሻጋሪ ወንጀሎችን በጋራ ለመከላከል መምከሩን ከፌዴራል ፖሊስ የተገኘው መረጃ አመልክቷል።

የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ የጀመረውን የቴክኖሎጂ ሽግግር፣ የሰው ኃይል አቅም ግንባታ፣ የፎረንሲክ እና የሳይበር ወንጀል ምርመራን አጠናክሮ ለማስቀጠል ከኢንተርፖል ጋር በትብብር መስራት በሚያስችሉ ሁኔታዎች ላይም ምክክር መካሄዱን በመግለጫው ተጠቁሟል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም