በሲዳማ ክልል ህብረተሰብን ያሳተፈ የሙስና መከላከል ተግባር ውጤት እያስገኘ ነው - ኮሚሽኑ

ሀዋሳ  ፤ ህዳር 19 /2016 (ኢዜአ)፡- በሲዳማ ክልል እየተካሄደ ባለው ህብረተሰብን ያሳተፈ የሙስና መከላከል ተግባር  ውጤት እያስገኘ  መምጣቱን የክልሉ የሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን አስታወቀ።

የክልሉ የሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽነር ወይዘሮ ዘላለም ለማ ዛሬ ማምሻውን በሰጡት መግለጫ እንዳመለከቱት፤ በክልሉ ህብረተሰብን በማሳተፍ እየተካሄደ ባለው የፀረ ሙስና ትግል ውጤት እየተመዘገበበት ነው።

ህብረተሰቡ የሚስተዋሉ የሙስናና ብልሹ አሰራሮችን የመጠቆምና አጋልጦ የመስጠት ልምዱ እየዳበረ መምጣቱን ጠቁመው፤ ይህም በክልል ደረጃ መልካም የሚባሉ ውጤቶች እንዲመዘገቡ ማድረጉን  ገልጸዋል።

ይህን ለማጠናከር እየተሰራ ነው ያሉት ኮሚሽነሯ፣ የህዝብን ንቃተ ህሊና ይበልጥ ለማጎልበትና ተሳትፎን ለማሳደግ ዓመታዊ የፀረ ሙስና ቀንን በተለያዩ ዝግጅቶች ማክበር ጠቀሜታ እንዳለው ጠቅሰዋል።

የዘንድሮው የፀረ - ሙስና ቀን "ሙስና የጋራ ጠላታችን ነው!" በሚል መሪ ሀሳብ በተለያዩ ዝግጅቶች እየተከበረ መሆኑን አመልክተው፤ በህዝባዊ ንቅናቄው ከቀበሌ እስከ ክልል ድረስ  የሙስና ትግልን የሚያጠናክሩ ሥራዎች እንደሚሰሩ ተናግረዋል።

ሙስና የልማት ሥራዎችን የሚያደናቅፍና ሰላምን የሚያውክ መሆኑን ያመለከቱት ኮሚሽነር ወይዘሮ ዘላለም፤ በፀረ ሙስና ትግሉ የህዝቡን ተሳትፎ ማጽናት እንደሚያስፈልግም አስታውቀዋል። 

ህብረተሰቡ በየአካባቢው የሚመለከተውን የሙስናን ችግር በግልጽ በማንሳትና ጥቆማ በመስጠት ለፀረ ሙስና ትግሉ የጀመረውን አጋርነት እንዲያጠናክርም ኮሚሽነሯ አሳስበዋል።

በክልሉ ከተቋቋመው የፀረ ሙስና ግበረ ኃይል ጋር በመቀናጀት ባለፈው ዓመት በተደረገ እንቅስቃሴ ውጤት መገኘቱንም አመልክተዋል።

ባለፈው ዓመት ለክልሉ ግብረ ኃይል ከህዝቡ 218 ጥቆማ መድረሱን ያስታወሱት ኮሚሽነሯ፤ ጥቆማውን መሠረት በማድረግ በተወሰደው አስቸኳይ ሙስናን የመከላከል እንቅስቃሴ ከ110 ሚሊዮን ብር በላይ የህዝብና የመንግሥት ሀብት ማዳን እንደተቻለም አስታውቀዋል።

በተጨማሪም በህገ ወጥ መንገድ ሊተላለፍ የነበረ 59 ሺህ ሄክታር የገጠር መሬት ወደ መሬት ባንክ ማስመለስ መቻሉን ተናግረዋል።

በማዳበሪያ ስወራና በሌሎች የሙስና ወንጀሎች የተጠረጠሩ 505 ሰዎች በቁጥጥር ስር ውለው ጉዳያቸው በ256 የክስ መዝገቦች በፍርድ ሂደት ላይ መሆኑን ጠቁመው፣ ከመካከላቸው የፍርድ ውሳኔ የተሰጣቸው እንዳሉም አብራርተዋል።

ኮሚሽነር ዘላለም እንዳሉት፤ በክልሉ 99 በመቶ የሚሆኑ የህዝብ ተመራጮች፣ ተሿሚዎች፣ የመንግስት ሠራተኞች፣ የልማት ድርጅቶች እና የህዝባዊ ድርጅቶች የሥራ ኃላፊዎችና ሠራተኞች ሃብታቸውን እንዲያስመዘግቡ ተደርጓል።

በመንግስት መስሪያ ቤቶች፣ የልማት ድርጅቶች እና በህዝባዊ ድርጅቶች ውሰጥ ለሙስናና ብልሹ አሰራር የተጋለጡ እና ሊጋለጡ የሚችሉ የአሰራር ስርዓቶችን እንዲጠኑ እንደሚደረግ ጠቅሰው፤ ኮሚሽኑ የሙስና ተጋላጭነት ችግርን ለመከላከል አበክሮ እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል። 

ለሙስና ተጋላጭ በሆኑ ተቋማት በተለዩ ችግሮች ላይ ምክረ ሀሳብ በመስጠት የተቋማት አመራር አባላት ችግሮችን እንዲያርሙና እንዲያስተካክሉ የመፍትሄ ሃሳብ እንደሚሰጣቸው የገለጹት ኮሚሽነሯ፣ ይህንን ተግባራዊ በማያደርጉት ላይ እርምጃ ለመውሰድ እየተሰራ መሆኑን አመልክተዋል።

ክልላዊ የዘንድሮ የጸረ ሙስና ቀን ማጠቃለያ መርሀ ግብር ህዳር 21 ቀን 2016 ዓም በይርጋለም ከተማ እንደሚካሄድ ታውቋል። 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም