ቀጥታ፡

ለብሔራዊ ባንክ የሚቀርበው የወርቅ ምርት እንዲጨምር በህገወጦች ላይ ጠንካራ እርምጃ እየተወሰደ ነው-የባንኩ ገዥ ማሞ ምህረቱ

አዲስ አበባ ፤ ህዳር 19/2016(ኢዜአ):-  ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የሚቀርበው የወርቅ ምርት እንዲጨምር  በህገወጦች ላይ  ጠንካራ እርምጃ እየተወሰደ መሆኑን የባንኩ ገዥ ማሞ ምህረቱ ገለጹ።

ለህጋዊ አምራቾች ማበረታቻ በመስጠት ለባንኩ የሚቀርበው የወርቅ ምርት እንዲጨምር  እየተሰራ መሆኑም ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክና ተጠሪ ተቋማት በ2016 በጀት  የባንክ የሩብ ዓመት አፈጻጸም ላይ ከህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የፕላን በጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ጋር ውይይት አድርገዋል።


 

የባንኩ ገዥ ማሞ ምህረቱ በዚሁ ጊዜ እንዳሉት፤ ወርቅ ለኢትዮጵያ ኢኮኖሚ የሚጫወተው ሚና ከፍተኛ ነው።

ከጥቂት ዓመታት በፊት ወርቅ ወደ ውጪ በመላክ እስከ 600 ሚሊዮን ዶላር ይገኝ እንደነበር አስታውሰው፤ በህገወጥ ንግድና በተለያዩ ችግሮች ገቢው እያሽቆለቆለ መጥቷል ብለዋል።

በተለይም ወርቅ አምራች በሆኑ አካባቢዎች የጸጥታ ችግር እንዲፈጠርና ሃብቱ በህገወጥ መንገድ እንዲወጣ በማድረግ አንዳንድ የመንግስት የስራ ሃላፊዎች ጭምር እጃቸው እንዳለበት ነው ያነሱት።

በመሆኑም ወደ ብሔራዊ ባንክ የሚቀርበው የወርቅ ምርት እንዲጨምር የክልል መንግስታት ጠንካራ ድጋፍ ሊያደርጉ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

አክለውም ባንኩ ከጸጥታና ደህንነት ተቋማት ጋር በመቀናጀት ህገወጥ የወርቅ ምርትና ግብይትን ለመቆጣጠር እየሰራ መሆኑን ጠቅሰው፤ በዚህም ጠንካራ እርምጃ እየተወሰደ ነው ብለዋል።

ማዕድናት በአግባቡ ተመርተው ለውጭ ገበያ እንዲቀርቡ የባለድርሻዎች የትብብር መድረክ መቋቋሙን ያነሱት የብሔራዊ ባንክ ገዥ፤ ለወርቅ አምራቾች እስከ 70 በመቶ ማበረታቻ በመስጠት የተሻለ ውጤት እየተገኘ መሆኑን ጠቅሰዋል።

የፕላን፣ በጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ደሳለኝ ወዳጆ በበኩላቸው፤ ብሔራዊ ባንክ የወርቅ ምርት በበቂ ሁኔታ ለማዕከላዊ ገበያ እንዲቀርብ ተጨማሪ መመሪያና ፖሊሲ ማውጣት አለበት ብለዋል።


 

ህገ-ወጥ የወርቅ ግብይትን ለመከላከልም ሌሎች ባለድርሻዎች ባንኩን ማገዝ እንዳለባቸው በመጠቆም።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የጥቁር ገበያ የውጭ ምንዛሬ መከላከል ላይ በልዩ ትኩረት ሊሰራ እንደሚገባም በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የፕላን በጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አሳስቧል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም