የፍትህ ትራንስፎርሜሽን ዕቅድን ለማሳካት የዘርፉ ባለድርሻ አካላት በትብብርና በቅንጅት ሊሰሩ ይገባል--ሚኒስቴሩ - ኢዜአ አማርኛ
የፍትህ ትራንስፎርሜሽን ዕቅድን ለማሳካት የዘርፉ ባለድርሻ አካላት በትብብርና በቅንጅት ሊሰሩ ይገባል--ሚኒስቴሩ
ጋምቤላ፣ ፤ ህዳር 19 /2016 (ኢዜአ)፡- በሀገሪቱ የተቀረጸውን የፍትህ ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ለማሳካት ሁሉም የዘርፉ ባለድርሻ አካላት በትብብርና በቅንጅት ሊሰሩ እንደሚገባ የፍትህ ሚኒስቴር አስታወቀ።
የጋምቤላ ክልል የፍትህ ቢሮ የትራንስፎርሜሽን ዕቅዱን ተግባራዊ ለማድረግ ባለፈው ሩብ ዓመት ያከናወናቸው ሥራዎች ዛሬ በጋምቤላ ከተማ ተገምግሟል።
በሚኒስቴሩ የተቋም ግንባታና ሪፎርም ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ኤርሚያስ የማነብርሃን በግምገማ መድረኩ ላይ እንዳሉት፣ ዜጎች ለሚያነሱት የፍትህ ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት የተቀረጸውን የትራስፎርሜሽን ዕቅድ በአግባቡ ተግባራዊ ማድረግ ይገባል ።
መንግስት ለሦስት ዓመት የሚተገበር የፍትህ ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ያዘጋጀው ከፍትህ ጋር ተያይዞ ከህዝብ ለሚነሱ የፍትህ ጥያቄዎች ምላሽ ለመስጠት በማለም መሆኑን ተናግረዋል።
ዕቅዱ የህዝቡን የፍትህ ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት አሳሪ የሆኑ የቆዩ ህጎች እንዲወጡ ተደርጎ የተዘጋጀ መሆኑንም ሚኒስትር ዴኤታው ገልጸዋል።
በመሆኑም ለዕቅዱ ስኬታማነት በተለይ ፍርድ ቤት፣ የፍትህ፣ የፖሊስ እና ሌሎች የዘርፉ ተቋማት በትብብርና በቅንጅት ሊሰሩ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
የኤፌዴሪ ፍትህ ሚኒስቴር ለዕቅዱ ስኬታማነት ለክልሎች የተጠናከረ ድጋፍ ለመስጠት ዝግጁ መሆኑንም አስታውቀዋል።
የጋምቤላ ክልል በመጀመሪያ ሩብ ዓመት ዕቅዱን ወደተግባር ለማሸጋገር ያደረገው የዝግጅት ምዕራፍና የሰው ኃይል አደረጃጀት የሚበረታታ መሆኑንም ሚኒስትር ዴኤታው ገልጸዋል።
የክልሉ ፍትህ ቢሮ ኃላፊ አቶ አኳይ አቡቲ በዚሁ ጊዜ እንዳሉት አዲሱን የፍትህ ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ተግባራዊ ለማድረግ የዘርፉ ተቋማት የተካተቱበት አብይና ንዑሳን ኮሚቴዎች በማቋቋም ወደ ሥራ ተገብቷል።
በመጀመሪያው ሩብ ዓመት በአብዛኛው የዝግጅት ምዕራፍ ሥራዎች መከናወናቸውን ጠቁመው በቀጣይ ከባለድርሻ አካላት ጋር ያለውን ቅንጅታዊ አሰራር ይበልጥ በማጠናከር ወደሙሉ ትግበራ ይገባል ብለዋል።
የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ ቻላ ኡጁሉ እና የክልሉ ፓሊሰ ኮሚሽን ኮሚሽነር ኮማንደር ኡማን ኡጋላ በበኩላቸው የተዘጋጀው የፍትህ ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ዜጎች ለሚያነሷቸው የፍትህ ጥያቄዎችና የአገልግሎት ጥራት ችግር ምላሽ የሚሰጥ ነው ብለዋል።
በመሆኑም ለዕቅዱ ስኬታማነትና በዘርፉ የታሰበውን የፍትህ አገልግሎትና ጥራት ለማሻሻል በትብብርና በቅንጅት እንደሚሰሩ አመራሮቹ ገልጸዋል።