የፌዴራል ስርዓቱ በአፋር ክልል የሴቶች ተሳታፊነትና ተጠቃሚነትን እያሳደገ ነው - አፈ ጉባኤ አሲያ ካሚል - ኢዜአ አማርኛ
የፌዴራል ስርዓቱ በአፋር ክልል የሴቶች ተሳታፊነትና ተጠቃሚነትን እያሳደገ ነው - አፈ ጉባኤ አሲያ ካሚል
ሰመራ ፤ ህዳር 19/2016(ኢዜአ) የፌዴራል ስርዓቱ በአፋር ክልል የሴቶችን ተሳታፊነትና ተጠቃሚነት እያደገ እንዲመጣ ማድረጉን የክልሉ ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባዔ አሲያ ካሚል አስታወቁ።
በክልሉ በተለያዩ አደረጃጀቶች ስር የሚገኙ ሴቶች 18ኛውን የብሄር፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ቀን በማስመልከት ዛሬ የፓናል ውይይት አካሂደዋል።
የክልሉ ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባዔ አሲያ ካሚል በውይይቱ ላይ እንዳሉት፤ ኢትዮጵያ የምትከተለው የፌዴራል ስርዓት የሴቶች ተሳታፊነትና ተጠቃሚነት እንዲጎለብት ያደረገ ነው ።
“በማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ዘርፎች ተጠቃሚነታቸውን ለማረጋገጥ እንዲቻል በር የከፈተ ነው” ሲሉ ተናግረዋል።
ሴቶች ሁለንተናዊ መብቶቻቸውን አውቀው ተጠቃሚ እንዲሆኑ ማስቻሉንም ገልፀዋል።
የክልሉ ሴቶችና ማህበራዊ ጉዳዮች ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ ኤይሻ ያሲን በበኩላቸው፤ በክልሉ በሚገኙ 20 ወረዳዎችና በአንድ የከተማ አስተዳደር ሴቶችን በማደራጀት ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን ገልፀዋል።
“የሴቶች ጉዳይ ለአንድ ተቋም ብቻ የሚተው አይደለም” ያሉት ኃላፊዋ፤ ሁሉም ሴቶች በተሠማሩበት መስክና ኃላፊነት ማገዝ እንደሚኖርበትም አመልክተዋል።
በፖናል ውይይቱ ፅሁፍ ያቀረቡት የክልሉ የፐብሊክ ስርቪስና የሰው ሃብት ልማት ቢሮ ምክትል ኃላፊ ወይዘሮ ነስሮ ኡዳ በበከላቸው፤ "ስርዓቱ ያመጣልንን ዕድሎች በደንብ ተጠቅመን ለሰላም ግንባታ አስተዋጽኦ ማድረግ ይኖርብናል" ብለዋል።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ሴቶች በትምህርትና በጤና ዘርፍ ተጠቃሚ እየሆኑ መምጣታቸውን ጠቅሰዋል።
"የፌዴራል ስርዓቱ የአፋር ሴቶች ከሌሎች እህቶቻችንና ወንድሞቻችን ጋር ህብረ ብሄራዊነታችንን አጉልቶ ያሳየ ነው" ያሉት ደግሞ የክልሉ የአካባቢ ጥበቃ፣ ገጠር መሬት አጠቃቀምና አስተዳደር ቢሮ ምክትል ኃላፊ ወይዘሮ ኩልሰማ ቡርሃባ ናቸው።
"ማንነታችን ላይ ተመርኩዘን ባህላችንን አስጠብቀን በጋራ ከመጓዝ አኳያ ላቅ ያለ አስተዋፅኦ አበርክቶልናል" ብለዋል ።
የአፋር ሴቶች ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ወይዘሮ ፋጡማ መሀመድ በበኩላቸው፤ የአፋር ሴቶች ከክልላቸው አልፎ በፌዴራል ደረጃ ተሳታፊ መሆን መቻላቸውን ጠቅስዋል።
ይህም በየደረጃው የሴቶችን ብቃትና የመሣተፍ አቅም ያረጋገጠና ይሁንታ የሰጠ መሆኑን ወይዘሮ ፋጡማ አመልክተዋል።
በአፋር ክልል ምክር ቤት አባልነት እንዲሁም በአመራር ደረጃ የሴቶች ተሳትፎ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ ስለመምጣቱ በፓናል ውይይቱ ተመላክቷል ።