ቀጥታ፡

በጋምቤላ የልማትና የብልጽግና ጉዞን እውን ለማድረግ በብዝሀነት ውስጥ አንድነት ማጠናከር ይገባል- አፈጉባኤ ባንቻየሁ ድንገታ

ጋምቤላ ፤ ህዳር 19/2016(ኢዜአ)፦ የጋምቤላ ክልልን የልማትና የብልፅግና ጉዞ እውን ለማድረግ በብዝሃነት ውስጥ ያለውን አንድነት ማጠናከር እንደሚገባ የክልሉ ምክር ቤት አፈ ጉባዔ ወይዘሮ ባንቻየሁ ድንገታ አሳሰቡ።

''ብዝሃነትና እኩልነት ለሃገራዊ  አንድነት!'' በሚል መሪ ሃሳብ 18ኛው የኢትዮጵያ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በዓል በክልል ደረጃ በኢታንግ ልዩ ወረዳ ዛሬ በሲምፖዚየም ተከብሯል። 


 

አፈ ጉባዔዋ በመድረኩ ላይ እንዳሉት በዓሉ በመፈቃቀድ ላይ የተመሰረተ አንድነትና ፍትሃዊ የልማት ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ ካለው ፋይዳ በተጨማሪ፣ ዴሞክራሲያዊና ሰብዓዊ መብቶችን በእኩልነት ለማስከበር ያስችላል ብለዋል። 

በዓሉ በመከባበር፣ በመቻቻልና በመፈቃቀድ ላይ የተመሠረተ መልካም ግንኙነትና አገራዊ አንድነትን ለማጠናከር ከፍተኛ  ሚና እንዳለውም አመልክተዋል፡፡ 

በተጨማሪም በዓሉ ከብዝሃነት ጋር ተያይዞ የሚነሱ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጥያቄዎች በኅብረ ብሔራዊነት ማዕቀፍ መልስ እንዲያገኙ አድርጓል ብለዋል።

በዓሉ ባለፉት 17 ዓመታት መከበሩ በህዝቦች መካከል ያለውን አንድነት ከማጠናከር ባለፈ የባህል ልውውጥ ለማድረግና እርስ በርስ ለመተዋወቅ አስተዋጾ ማድረጉን ወይዘሮ ባንቻየሁ ተናግረዋል። 

በዓሉ በተለይም የክልሉን እምቅ ባህላዊ እሴቶችና የተፈጥሮ ሀብቶችን በማስተዋወቅ በኩልም መልካም ዕድሎች መፍጠሩን ነው አፈ-ጉባኤዋ ያስታወቁት። 

በአገረ መንግስት ግንባታ ሂደትም በህግና ስርዓት የሚመራ ነፃና ገለልተኛ ተቋማትን ለመገንባት ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑንም ገልጸዋል። 

የክልሉ ምክር ቤት የሕግ፣ ፍትህና  ዴሞክራሲ  ጉዳይ ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ኡጁሉ ኝጉዎ ባቀረቡት የመወያያ ጽሁፍ እንዳሉት፣ በኅብረ-ብሔራዊ ፌዴራሊዝም ሥርዓት ጠንካራ ሃገረ መንግስት በመገንባት ረገድ አበረታች ሥራዎች ተከናውነዋል። 

እንደ ሀገር እያጋጠሙ ያሉ ፈተናዎችን በድል ለመሻገርና የኢትዮጵያን ከፍታ ለማረጋገጥ ሁሉም የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች  ልንረባረብ ይገባናል ብለዋል። 

በክልል ደረጃ  የበዓሉ ማጠቃለያ ነገ በኢታንግ ልዩ ወረዳ በድምቀት እንደሚከበር  የበአሉ  መርሃ ግብር ያመላክታል።

የዘንድሮው የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን ኅዳር 29 ቀን 2016 በሶማሌ ክልል ጅግጅጋ ከተማ  እንደሚከበር ይታወቃል።

በዓሉ በተያዘው ወር በክልሎችና በሁለት የከተማ አስተዳደሮች የሚገኙ የአስተዳደር መዋቅሮችና ተቋማት በተለያዩ ዝግጅቶች እያከበሩት ነው።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም