ቀጥታ፡

በዓሉ የብሔር ብሔረሰቦችን ባህልና ከማስተዋወቅ ባለፈ የእርስ በርስ ግንኙነትን እያጠናከረ ነው

ሮቤ፤ ህዳር 19/2016 (ኢዜአ)፡- የብሔር ብሔረሰቦች እና ህዝቦች በዓል የብሔረሰቦችን ባህልና እሴት በአደባባይ ከማስተዋወቅ ባለፈ የእርስ በርስ ግንኙነትን እያጠናከረ መሆኑን የመደ ወላቡ ዩኒቨርስቲ ተማሪዎችና ሰራተኞች ገለጹ። 

የመደ ወላቡ ዩኒቨርሲቲ ማህበረሰብ 18ኛውን የብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች በዓል ''ብዝሃነት እና እኩልነት ለአገራዊ አንድነት'' በሚል መሪ ሐሳብ በፅዳትና በደም ልገሳ መርሃ ግብር አክብረዋል። 

የዩኒቨርሲቲው ተማሪዎችና ሠራተኞች በዚሁ ጊዜ እንዳሉት "በዓሉ በብዝሃነት ውስጥ አብሮነትና እኩልነትን የምናጎለብትበት ነው። 

አስተያየታቸውን ለኢዜአ ከሰጡ የዩኒቨርሲቲው ተማሪዎች መካከል ሃሊማ ቢቂላ  እንዳለችው በዓሉ የብሔር ብሔረሰቦችን ባህልና እሴት በአደባባይ ከማስተዋወቅ ባለፈ "እርስ በርስ ያላቸውን ግንኙነት እያጠናከረ ነው"። 

የዘንድሮ የብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች በዓል በዩኒቨርሲቲው ውስጥ በተለያዩ ዝግጅቶች በድምቀት እያከበሩት በመሆናቸውም ደስተኞች እንደሆኑም አመልክታለች። 

ሌላው የበዓሉ ተሳታፊ ተማሪ ደራራ አብዲ በበኩሉ ባለፉት ሶስት ዓመታት በዓሉን በተለያዩ ዝግጅቶች በዩኒቨርሲቲው ውስጥ ሲያከብሩ መቆየታቸውን አስታውሷል።

በዓሉ በተለይም ከተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች የመጡ ተማሪዎች የእርስ በርስ ታሪክና ባህልን በመለዋወጥ አብሮነታቸው እንዲጎለብት ማድረጉን ገልጿል። 

በዓሉ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ውስጥ መከበሩ አንድነትንና መከባበርን ከማጎልበት ባለፈ ለሰላማዊ የመማር ማስተማር ሥራው ውጤታማነት የጎላ ድርሻ እንዳለውም አመልክቷል። 

''በዓሉ በብዝሃነት ውስጥ አንድነት የሚደምቅበትና የጋራ እሴቶችና አንድነታችንን የምናጠናክርበት ነው'' ያለው ደግሞ የዩኒቨርሲቲው መምህር አብዱልፈታህ አብዱ ነው።

የመደ ወላቡ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ተወካይ አቶ ደጀኔ ጣፋ በበኩላቸው፣ ዩኒቨርሲቲዎች የኢትዮጵያ ብሔሮችና ብሔረሰቦች ባህል፣ማንነትና ትውፊት የሚጎላበት ነጻብራቅ ናቸው ብለዋል። 

ኢትዮጵያኖች በመቻቻል፣ በመረዳዳት እና በአብሮነት ለዘመናት መኖራቸውን አስታውሰው፣ ይሄ እሴት ሳይበረዝ በቀጣይም ተጠናክሮ መቀጠል ይገባል ብለዋል። 

የብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች አብሮነትና አንድነታቸው መጠናከር ለአገራዊ እድገትና ትልም ስኬት ጉልህ ድርሻ ስለሚኖረው በተለይም ምሁራን በዘርፉ የሚታዩ ተግዳሮቶችን ነቅሰው ለማውጣት ምርምር በማካሄድ ተሳትፏቸውን እንዲያጠናክሩ አስገንዝበዋል። 

የዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ ቀኑን ምክንያት በማድረግ የግቢ ውስጥ ፅዳትና የደም ልገሳ በማካሄድ አክብረዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም