የኤሌክትሮኒክስ የመንግስት ግዥ የአሰራር ሥርዓት ብክነትን በማስወገድ ፍትሃዊነት እንዲረጋገጥ ያደርጋል - ኢዜአ አማርኛ
የኤሌክትሮኒክስ የመንግስት ግዥ የአሰራር ሥርዓት ብክነትን በማስወገድ ፍትሃዊነት እንዲረጋገጥ ያደርጋል

ሀዋሳ፤ህዳር 19/2016 (ኢዜአ)፡- ፍትሃዊና ለብክነት ያልተጋለጠ የግዥ አሰራርን ለመዘርጋት የኤሌክትሮኒክስ የግዥ ሥርዓት በሁሉም ደረጃ ባሉ የመንግስት ተቋማት እንዲተገበር እየተሰራ መሆኑን የመንግስት ግዥና ንብረት ባለሥልጣን ገለፀ ፡፡
የሲዳማ ክልል ፋይናንስ ቢሮ ከመንግስት ግዥና ንብረት ባለሥልጣን ጋር በመተባበር በኤሌክትሮኒክስ የመንግስት ግዥ የአሰራር ሥርዓት ላይ ለአቅራቢዎች የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥልጠና ሰጥቷል ፡፡
በመርሃ ግብሩ ላይ የተገኙት የመንግስት ግዥና ንብረት ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ሃጂ ኢብሳ የኤሌክትሮኒክስ የመንግስት ግዥ ከሌሎች ሀገራት ልምድ በመውሰድ በኢትዮጵያ ከ2014 ዓ.ም ጀምሮ ገቢራዊ የሆነ የግዥ ሥርዓት እንደሆነ ተናግረዋል ፡፡
የአሰራር ሥርዓቱ በተለይ በመንግስት ግዥዎች ላይ ፍትሐዊነትን በማረጋገጥ ለብክነት ያልተጋለጠ ሂደትን በማስፈን ረገድ የጎላ ሚና እንዳለው ተናግረው በሁሉም ደረጃ ባሉ የመንግስት ተቋማት ላይ ተግባራዊ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን ገልፀዋል ፡፡
በ2014 ዓ.ም ትግበራው ሲጀመር በዘጠኝ የፌዴራል ተቋማት ላይ መሆኑን አውስተው አሁን ላይ 169 የፌዴራል ተቋማት ወደ አሰራር ሥርዓቱ ገብተዋል ብለዋል ፡፡
በክልሎች ደግሞ ለመጀመሪያ ጊዜ በሲዳማ ክልል በተመረጡ ዘጠኝ ተቋማት ወደ ሥርዓቱ እንዲገቡ በሙከራ ደረጃ መጀመሩን ጠቅሰዋል ፡፡
በፌዴራል ደረጃ እስካሁን ከ38 ሺህ ባለይ የሚሆኑ የንግዱ ማህበረሰብ አባላት በዚህ አሰራር ዙሪያ ሥልጠና እንደተሰጣቸውም ጠቁመዋል ፡፡
የንግዱ ማህበረሰብ በዚህ የአሰራር ሥርዓት የመንግስት ጨረታዎችን በተመለከተ በቀላሉ መረጃ ከማግኘት ባሻገር የሚወዳደሩትም በኤሌክትሮኒክስ ሥርዓት በመሆኑ ጊዜና ወጪያቸውን በከፍተኛ ደረጃ እንደሚቀንስላቸው አስረድተዋል ፡፡
ሥርዓቱ መንግስት በግዥ ሂደት ውስጥ የሚፈፀምን ሌብነትና አድሏዊ አሰራሮችን በመከላከል ፍትሐዊነትና ግልፀኝነትን ማረጋገጥ የሚያስችለው አሰራር እንደሆነ ጠቁመዋል ፡፡
''ፍትሃዊነት በገንዘብ የማይተመን ነው'' ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ፤ ከወጪ አኳያ ባለው ዓለም አቀፍ ተሞክሮ በዚህ የአሰራር ሥርዓት ሀገራት ከ5 እስከ 25 በመቶ ዓመታዊ በጀታቸውን መቆጠብ እንደቻሉም አብራርተዋል ፡፡
የሲዳማ ክልል ፋይናንስ ቢሮ ሃላፊ ዶክተር አራርሶ ገረመው በክልሉ ለጅማሮ ዘጠኝ ክልላዊ ተቋማት ወደዚህ ሥርዓት እንደሚገቡ ገልፀዋል ፡፡
በቀጣይ በሁሉም ደረጃ ያሉ የመንግስት ተቋማት ወደ ሥርዓቱ እንደሚገቡም ጠቁመዋል ፡፡
ከዓመታዊ የክልሉ በጀት ከ60 በመቶ በላይ የሚውለው ለግዥ ነው ያሉት ኃላፊው ይህን ያህል ሀብት የሚዘዋወርባቸው የመንግስት ግዥዎች ከአድሎና ኢፍትሐዊ አሰራር ነፃ እንዲሆኑ ማድረግ ለሁሉም አካላት አስተዋፅኦው ከፍተኛ ነው ብለዋል፡፡
ከዚህ በፊት የመንግስት ግዥ ጨረታዎች ሲወጡ ረጅም ጊዜን እንዲሁም የወረቀትና ሌሎች ወጪዎችን እንደሚጠይቁ አስታውሰው ይህንን የሚያስቀር አሰራር ነው ብለዋል ፡፡
በሥልጠናው ከተሳተፉ የንግዱ ማህበረሰብ አባላት መካከል በግንባታ ተቋራጭነት ዘርፍ ላይ የተሰማሩት አቶ ጎበዛየሁ ፋንታ "የኤሌክትሮኒክስ ግዥ ዘመናዊ የጨረታ ሥርዓት እንዲኖር በማድረግ ሥራዎቻችንን ቀላል የሚያደርግ ነው" ብለዋል ፡፡
ወጪያችንን በመቆጠብና ከአድሎ ነፃ የሆነ ውድድር እንዲኖር መደላድልን በመፍጠር ረገድ ጠቀሜታው ከፍተኛ በመሆኑ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ተባብረን በመስራት የሚጠበቅብንን እንወጣለን ብለዋል ፡፡
በስልጠናው ላይ የፌዴራልና የክልል ከፍተኛ የሥራ ሃላፊዎች የተገኙ ሲሆን ከ260 በላይ የሚሆኑ አቅራቢዎች ተሳትፈዋል፡፡