የብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች በዓል በየዓመቱ መከበሩ ህብረ-ብሔራዊ አንድነት እንዲጎለብት ትልቅ ፋይዳ አለው - ኢዜአ አማርኛ
የብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች በዓል በየዓመቱ መከበሩ ህብረ-ብሔራዊ አንድነት እንዲጎለብት ትልቅ ፋይዳ አለው
ቦንጋ ፤ ህዳር 19/2016(ኢዜአ): የብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች በዓል በየዓመቱ መከበሩ ህብረብሔራዊ አንድነት እንዲጎለብት ከማድረግ አንጻር ትልቅ ፋይዳ እንዳለው ተገለጸ፡፡
"ብዝሃነትና እኩልነት ለሀገራዊ አንድነት" በሚል መሪ ሃሳብ የዘንድሮው 18ኛው የብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን በቦንጋ ዩኒቨርሲቲ በተለያዩ ዝግጅቶች እየተከበረ ነው ፡፡
በመድረኩ ላይ የቦንጋ ዩኒቨርሲቲ አካዳሚክ ፕሮግራሞች ዳይሬክተር ዶክተር ዬሪቾ ብርሃኑ እንዳሉት የብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች ቀን በየዓመቱ መከበሩ ህብረ ብሄራዊ አንድነት እንዲጎለብት ከማድረግ አንጻር ትልቅ ፋይዳ አለው፡፡
በዓሉ የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች እርስ በርስ የሚተዋወቁበትን መድረክ ከመፍጠሩም ባሻገር የተለያዩ ማንነቶች፣ ቱባ ባህሎች፣ ቋንቋና የአኗኗር ዘይቤ ጎልቶ የሚወጣበት መሆኑ ከሌሎች በዓላት ልዩ ያደርገዋል ብለዋል።
ዩኒቨርሲቲያችን እንደ ሌሎች ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ሁሉ የተለያዩ የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች መገኛ ነው ያሉት ዶክተር ዬሪቾ፣ እንደዚህ ዓይነት በዓል መከበሩ ብሄራዊ መስተጋብርና አንድነትን ለማሳየት ሚናው የጎላ ነው ያሉት ፡፡
በዓሉን ከተማሪዎችና ከዩኒቨርሲቲው የማህበረሰብ አባላት ጋር በየዓመቱ እየተከበረ እንደሚገኝ ገልጸው የዘንድሮም በተመሳሳይ በሀገር አቀፍ ደረጃ የሚገኙ የማንነትና የባህል ሀብቶችን በማቅረብ እየተከበረ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
''የ18ኛውን የብሄር ብሄረሰቦችና ሕዝቦችን ቀን ስናከብር የህዝቡን የረጅም ዘመን የአብሮነት ታሪክና ትስስርን በማጠናከር ሕብረ-ብሔራዊ አንድነት ሥር እንዲሰድና እንዲዳብር በማድረግ ሊሆን ይገባልም'' ብለዋል፡፡
የነገ የሃገር ተስፋ የሆኑ ተማሪዎች በዓሉን ማክበር ብቻ ሳይሆን ታላቋን ኢትዮጵያ ለመገንባት ቃል የሚገቡበትና ራሳቸውን የሚያዘጋጁበት ሊሆን እንደሚገባ ዶክተር ዬሪቾ ጥሪ አቅርበዋል።
በዓሉ በፓናል ውይይትና በተለያዩ ዝግጅቶች እየተከበረ ሲሆን የዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ እና ተማሪዎች እየታደሙበት ነው።
የኢፌዲሪ ሕገ መንግስት የፀደቀበት 1987 ዓም ህዳር 29/ቀን በየዓመቱ የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን ሆኖ እንዲከበር የፌዴሬሽን ምክር ቤት መወሰኑን ተከትሎ ላለፉት አስራ ሰባት ዓመታት ሲከበር መቆየቱም ይታወሳል፡፡
የዘንድሮው የ18ኛው የብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች ቀን በሶማሌ ክልል ጅግጅጋ ከተማ መጪው ህዳር 29 ቀን 2016 ዓም በታላቅ ድምቀት ለማክበር በሁሉም አካባቢዎች ቅድመ ዝግጅቶች እየተደረጉ እንደሆነ ይታወቃል፡፡