በትምህርት ዘርፉ የተጀመሩ የለውጥ ስራዎች የሚፈለገውን ውጤት ለማምጣት ትልቅ ተስፋ የሰጡ ናቸው- ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ - ኢዜአ አማርኛ
በትምህርት ዘርፉ የተጀመሩ የለውጥ ስራዎች የሚፈለገውን ውጤት ለማምጣት ትልቅ ተስፋ የሰጡ ናቸው- ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ
አዲስ አበባ፤ ህዳር 19/2016(ኢዜአ):- በትምህርት ዘርፉ ጥራትን ለማስጠበቅ የተጀመሩ የለውጥ ስራዎች የሚፈለገውን ውጤት ለማምጣት ትልቅ ተስፋ የሰጡ መሆናቸውን የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ ገለጹ።
በጅግጅጋ ከተማ ሲካሄድ የቆየው 32ኛው ሀገር አቀፍ የትምህርት ጉባዔ በዛሬው ዕለት ተጠናቅቋል።
በጉባዔው በተለይም በትምህርት ዙሪያ ሰፊ ውይይት የተደረገ ሲሆን ለዘርፉ ልማት የሚጠቅሙ ውሳኔዎችን በማሳለፍና ባለ 11 ነጥብ የጋራ የአቋም መግለጫዎችን በማውጣት ተጠናቋል።
በጉባኤው ማጠቃለያ ላይ ንግግር ያደረጉት የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ፤ መድረኩ በርካታ ጠቃሚ ግብአቶች የተገኙበትና ለዘርፉ እድገት የጋራ አቋም የተያዘበት መሆኑን ገልጸዋል።
የትምህርት ዘርፉን ማነቆዎች በትብብር በአጭር ጊዜ መፍትሔ ለመስጠት ሙሉ ተነሳሽነት የታየበት መሆኑንም ጠቅሰዋል።
ሚኒስትሩ በንግግራቸው 32ኛው የትምህርት ጉባኤ በትምህርቱ ዘርፍ የታየውን ስብራት መጠገን የሚያስችል ስንቅ የተገኘበት መልካም አጋጣሚ መሆኑንም አንስተዋል።
በትምህርት ዘርፉ ጥራትን ለማስጠበቅ የተጀመሩ የለውጥ ስራዎች ውጤት ለማምጣት ትልቅ ተስፋ የሰጡ መሆናቸውን ተናግረዋል።
በትምህርት ዘርፉ ላይ የተጀመረው የለውጥ ስራ የኢትዮጵያ የወደፊት ተስፋ ብሩህ መሆኑን ያመለከተና ለትውልድ ግንባታ ጥሩ መሰረት የጣለ መሆኑንም ገልጸዋል።
ከመድረኩ ተሳታፊዎች መካከል ኢዜአ ያነጋገራቸው የሀረሪ ክልል ትምህርት ቢሮ ሃላፊ ከድር ካሊ፣ የደብረብርሃን ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር ንጉስ ታደሰ ጉባኤው የትምህርት ስርዓቱ መሻሻል ጠቃሚ ግብአት የተገኘበት ነው ብለዋል።
ለዘመናት በትምህርት ስርዓቱ ላይ የደረሰውን ስብራት በመጠገን የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ ሁሉም የበኩሉን እንዲወጣ የጋራ መግባባት ላይ የተደረሰበት መሆኑንም ገልጸዋል።