የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ከ249 ቢሊየን ብር ብላይ ገቢ አገኙ

አዲስ አበባ፤ ህዳር 19/2016(ኢዜአ): የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግ የሚያስተዳድራቸው የመንግሥት የልማት ድርጅቶች በሩብ ዓመቱ ከ249 ቢሊየን ብር ብላይ ገቢ ማግኘታቸው ተገለጸ።

የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግ ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚ ያስሚን ወሀብረቢ፤ ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ በ2016 በጀት የመጀመሪያ ሩብ ዓመት የልማት ድርጅቶች የተሻለ አፈጻጸም ማስመዝገባቸውን ገልፀዋል።

ድርጅቶችን በዓለም አቀፍ የትርፋማ ቢዝነስ ሞዴል እንዲመሩ ሰፊ የለውጥ ሥራዎች መከናወኑን  ጠቅሰው፤ በዚህም ወደ ከፍተኛ ትርፋማነት መሸጋገራቸውን ነው ያነሱት።

ለአብነትም በ2015 በጀት ዓመት ከ924 ቢሊየን ብር በላይ ገቢ ማግኘታቸውን አስታውሰው፤ ከዚህም ከታክስ በፊት 118 ቢሊየን ብር ትርፍ ማስመዝገባቸውን ነው ያስረዱት።

በ2016 የመጀመሪያ ሩብ ዓመት ደግሞ 249 ቢሊየን ብር ገቢ ከልማት ድርጅቶች መገኘቱን ያነሱት ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚዋ፤ ከባለፈው ተመሳሳይ ወቅት የ43 በመቶ ጭማሪ ማሳየቱን ገልፀዋል።

ከታክስ በፊት 35 ቢሊየን ብር ትርፍ ማስመዝገባቸውን በመጥቀስ።

በሩብ ዓመቱ የኢትዮጵያ አየር መንገድ፣ ኢትዮ-ቴሌኮም፣ የባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ፣ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የላቀ አፈጻጸም ያስመዘገቡ ድርጅቶች መሆናቸውን ጠቅስዋል።

በሌላ በኩል የስኳር ፋብሪካዎች፣ ፐልፕና ወረቀት እንዲሁም የማዕድን ኮርፖሬሽን አሁንም በኪሳራ ላይ መሆናቸውን ጠቅሰው፤ ሆኖም የኪሳራ መጠናቸው ከዓመት ወደ ዓመት እየቀነሰ መምጣቱን ገልፀዋል።

የስኳር ፋብሪካዎች በ2014 በጀት ዓመት ያስመዘገቡት ኪሳራ 5 ቢሊየን ብር እንደነበር አስታውሰው፤ በ2015 በጀት ዓመት ግን ወደ ግማሽ ቢሊየን ማውረድ ተችሏል ነው ያሉት።

እነዚህን ድርጅቶች ሙሉ ለሙሉ ከዕዳ በማላቀቅ ወደ ትርፋማነት ለማሸጋገር የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግ ቦርድ የኩባንያ የሽግግር ፕሮግራም ማጽደቁን ገልፀዋል።

በኪሳራ ላይ የሚገኙትን ከዓለም አቀፍ በተገኘው ተሞክሮ መሠረት በአጭር ጊዜ ውስጥ ወደ ተሻለ ምዕራፍ እንዲለወጡ ልዩ ትኩረት ይደረጋል ብለዋል።

በአንጻሩ በትርፋማነት ላይ የሚገኙ ኩባንያዎች ደግሞ ተጨማሪ የኢንቨስትመንት ማስፋፊያ ላይ እንዲገቡ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግ የሚያስተዳድራቸው ኩባንያዎች አጠቃላይ ኃብት ከ2 ነጥብ 4 ትሪሊዮን ብር በላይ መድረሱ ታውቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም