ቀጥታ፡

"ፌም-ዋይዝ " የተሰኘው የአፍሪካ የሴቶች የሰላም ትስስር በኢትዮጵያ ሥራውን ጀመረ

አዲስ አበባ፤ ህዳር 19/2016(ኢዜአ):-በአፍሪካ ሕብረት ጥላ ሥር የሚንቀሳቀሰው "ፌም-ዋይዝ " የተሰኘው የአፍሪካ የሴቶች የሰላም ትስስር በኢትዮጵያ ሥራውን ጀመረ። 

በግጭት መከላከልና በሰላም ድርድር ላይ የሚሰሩ የአፍሪካ ሴቶች ትስስር (ፌም ዋይዝ አፍሪካ) እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ2017 በአፍሪካ ሕብረት ጠቅላላ ጉባዔ የሰላምና ደኅንነት አርክቴክቸር አንዱ ምሰሶ የሆነው የልሂቃን የምክክር መድረክ የአሠራር ሥርዓት ሆኖ ነው የተቋቋመው።

ትስስሩ በዋናነት የአቅም ማጎልበቻ፣ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራ እንዲሁም ልምድ መለዋወጫ መድረኮችን በማዘጋጀት ሴቶች በግጭት መከላከል እንዲሁም በሰላም ድርድር ያላቸውን አቅም ለማጎልበት እየሰራ ይገኛል። 

ትስስሩ ሥራውን በኢትዮጵያ በይፋ የማስጀመር መርኃ-ግብር ዛሬ በአፍሪካ ሕብረት ተካሂዷል፤ ይህንንም ተከትሎ ለቀጣይ ሁለት ወራት በኢትዮጵያ በዘርፉ ከሚሰሩ ሴቶች ጋር ትስስር ለመፍጠርና የአቅም ማጎልበቻ መርኃ-ግብር እንደሚኖርም ተጠቁሟል።  

የሰላም ሚኒስትሩ ብናልፍ አንዷለም በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት፤ ኢትዮጵያ በአፍሪካ ለሚደረጉ የሰላም ተልዕኮዎች ከፍተኛ አስተዋጽዖ እያደረገች ያለች አገር ናት።


 

እነዚህ ተልዕኮዎች አሁን ላይ ወደ ሰላም ግንባታ መሸጋገር እንዳለባቸው ገልጸው፤ እንደ ፌም ዋይዝ አፍሪካ የመሳሰሉ እንቅስቃሴዎች ይህንን ለማሳካት ወሳኝ መሆናቸውን ገልፀዋል።

የኢትዮጵያ መንግሥት ሴቶች በሰላም ግንባታ ላይ ያላቸው ሚና እንዲጎለብት በቁርጠኝነት እየሰራ መሆኑን ጠቁመው፤ ፌም ዋይዝ ይህንኑ የሚደግፍ መሆኑን ተናግረዋል። 

የሰላም ሚኒስትር ዴኤታ ታዬ ደንደአ በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያ ወደዚህ ትስስር መቀላቀሏ በሰላም ግንባታ ውስጥ የሴቶችን ሚና ከፍ ለማድረግ እንደሚያስችል ጠቁመዋል።


 

ትስስሩ የልምድ ልውውጥና የመማማር መንፈስን ያዳብራል ያሉት ደግሞ በአፍሪካ ሕብረት የሽምግልናና ውይይት ዲቪዥን ኃላፊ ዶክተር አኮክ ማዱት ናቸው።


 

እንቅስቃሴዎቹ የሰላም ጥረቶች ተጨባጭ ለውጥ እንዲያመጡ ትልቅ አስተዋጽዖ ያበረክታሉ ብለዋል።

ፌም ዋይዝ አፍሪካ አሁን ላይ 465 አባላት ያሉት ሲሆን፤ ከዚህ ቀደም ዩጋንዳና ማላዊ ላይ ተመሳሳይ የማስጀመሪያ መርኃ-ግብር ተካሂዷል።  

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም