ቀጥታ፡

የሀገር እድገት ማነቆና የኢኮኖሚ ድቀት ምክንያት የሆነውን የሙስና ወንጀል ሁላችንም ከወዲሁ መታገል አለብን

አዲስ አበባ ፤ ህዳር 19 /2016(ኢዜአ)፡- የሀገር እድገት ማነቆና የኢኮኖሚ ድቀት ምክንያት የሆነውን የሙስና ወንጀል ሁላችንም ከወዲሁ መታገል ይጠበቅብናል ሲሉ የመስኖና ቆላማ አካባቢ ሚንስትር ኢንጅነር አይሻ መሀመድ ተናገሩ።

የመስኖና ቆላማ አካባቢ ሚኒስቴር ሰራተኞች ዓለም ዓቀፍ የፀረ- ሙስና ቀንን "ሙስና የጋራ ጠላታችን ነው፤ በኅብረት እንታገል!" በሚል መሪ ሃሳብ አክብረዋል።

በመድረኩ የሙስና ወንጀልና ተያያዥ ችግሮች በሀገርና ህዝብ ላይ ሊያስከትል የሚችለውን ጉዳት በሚመለከት የመነሻ ጽሁፍ ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል።


 

በመድረኩ ላይ የተገኙት የመስኖና ቆላማ አካባቢ ሚኒስትር ኢንጅነር አይሻ መሀመድ፤ በኢትዮጵያ የተጀመሩ የልማት ስራዎችን ከዳር ለማድረስ ሙስናን መታገል ይገባል ብለዋል።

በተለይም በሚኒስቴሩ የሚመሩ በርካታ የልማት ፕሮጀክቶች ጥራታቸውን ጠብቀው እንዲከናወኑ በመስራት ግደታችንን እንወጣለን ሲሉ አረጋግጠዋል።

የሀገር የእድገት ማነቆና የኢኮኖሚ ድቀት ምክንያት የሆነውን የሙስና ወንጀል በመከላከል የዜጎችን ኑሮ ለማሻሻል መስራት የጋራ ጥረትን የሚጠይቅ በመሆኑ ሁላችንም ወንጀሉን እንታገል ሲሉ መልእክታቸውን አስተላልፈዋል። 

በተቋሙ የሚከናወኑ የልማት ስራዎችን የሙስና ተጋላጭነት ለመግታት ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር እየሰራን ነው ያሉት ሚኒስትሯ የዘመኑ አሰራሮችን ተግባራዊ በማድረግ ላይ እንገኛለንም ብለዋል።

በፌዴራል የሥነ-ምግባርና የፀረ-ሙስና ኮሚሽን የስነ ምግባርና ጸረ ሙስና ስልጠና መሪ ስራ አስፈጻሚ አቶ ዳግም አላምረው፤ ኮሚሽኑ ለሙስና ተጋላጭ ሊሆኑ ይችላሉ ያላቸውን ተቋማት በመለየት የመከላከል ተግባራትን እያከናወነ መሆኑን ገልጸዋል።


 

በተለይም የግዥ፣ የፕሮጀክት ግንባታ አስተዳደር እና የአገልግሎት አሰጣጥ ፍትሀዊነት ላይ በትኩረት እየተሰራ ስለመሆኑ ጠቅሰዋል።

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም