የጅማ ከተማ ነዋሪዎች ለታላቁ ህዳሴ ግድብ ድጋፍ የ20 ሚሊዮን ብር ቦንድ ገዙ - ኢዜአ አማርኛ
የጅማ ከተማ ነዋሪዎች ለታላቁ ህዳሴ ግድብ ድጋፍ የ20 ሚሊዮን ብር ቦንድ ገዙ
ጅማ፤ ህዳር 19/2016 (ኢዜአ) ፡- የጅማ ከተማ ነዋሪዎች በአንድ ቀን ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ፕሮጀክት ማጠናቀቂያ ድጋፍ የ20 ሚሊዮን ብር የቦንድ ግዢ ፈጸሙ።
ዛሬ በጅማ ከተማ ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ህብረተሰቡ በሁሉም የከተማው ቀበሌዎች የቦንድ ግዢ በዘመቻ መልክ አከናውነዋል።
በጅማ ከተማ የታላቁ ህዳሴ ግድብ የቦንድ ሽያጭ አስተባባሪ አቶ ጅሃድ ሁሴን እንዳሉት በዚህ ዙር ከከተማው ነዋሪዎች 28 ሚሊዮን ብር ለመሰብሰብ ታቅዶ ዛሬ በተካሄደው እንቅስቃሴ የ20 ሚሊዮን ብር የቦንድ ሽያጭ ተከናውኗል።
የከተማው ነዋሪ የህዳሴ ግድቡ ግንባታ ከተጀመረ ጊዜ አንስቶ በንቃት ሲሳተፍ እንደነበረ ገልጸው አሁንም የቦንድ ግዢውን እየፈጸመ መሆኑን ገልጸዋል።
የከተማው ህብረተሰብ ለወደፊቱም በህዳሴው ግድብ ጉዳይ ለመተባበርና ለመሳተፍ ፍቃደኛ መሆኑን ገልጸው የማስተባበር ስራውም ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።
በቦንድ ግዥው ከተሳተፉ የጅማ ከተማ ነዋሪዎች መካከል ወይዘሮ ሉባባ መሐመድ በዚሁ ጊዜ እንዳሉት በእስካሁኑ የግድቡ ግንባታ ደረጃ ተሳትፎ ሲያደርጉ ቆይተዋል።
ዛሬም የአንድ ሺህ ብር ቦንድ በመግዛት ድጋፋቸውን እንደቀጠሉ ገልጸው ለኢትዮጵያ ትልቁ ሀብት ለሆነው ግድባችን ለመተባበር አሁንም ዝግጁ መሆናቸውን ገልጸዋል።
"ለታላቁ የህዳሴ ግድብ መጠናቀቅ ሁላችንም ኢትዮጵያውያን በትብብር መስራት እና ለታቀደለት አላማ ማድረስ አለብን" ሲሉም ተናግረዋል።
ሌላው በቦንድ ግዢው የተሳተፈው ወጣት ኢዘዲን አባድር በበኩሉ ''እኔ እንደ ወጣት ለህዳሴ ግድቡ ግንባታ የበኩሌን ለመወጣት የ5ሺህ ብር ቦንድ ገዝቻለው'' ብሏል።
"እኛ ወጣቶች ለሀገር እድገት እና ልማት ጉልህ አስተዋጽኦ ላለው የህዳሴ ግድቡ ግንባታ በግንባር ቀደምነት አስፈላጊ ነው" ሲልም ተናግሯል።