ቀጥታ፡

የክልሉን የብዝሃነት ፀጋዎች ለእድገትና ለዘላቂ ልማት ልንጠቀምበት ይገባል- የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ምክር ቤት

ዲላ፤ ህዳር 19/2016 (ኢዜአ)፡-  ብዝሃነታችን ያጎናጸፈንን ፀጋዎች ለክልሉ እድገትና ዘላቂ ልማት ልንጠቀም ይገባል ሲሉ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ምክር ቤት ምክትል አፈ-ጉባኤ ወይዘሮ ወላይቴ ቢቶ ተናገሩ። 

''ብዝሃነትና እኩልነት ለሀገር እድገት'' በሚል መሪ ቃል እየተከበረ የሚገኘው 18ኛው የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በጌዴኦ ዞን ዲላ ከተማ በተለያዩ መርሃ ግብሮች በድምቀት ተከብሯል።

የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ምክር ቤት ምክትል አፈ-ጉባኤ ወይዘሮ ወላይቴ ቢቶ በመድረኩ እንዳሉት፤ በሀገራችን በብዝሃነት ውስጥ አንድነታችንንና ወንድማማችነትን በማጉላት የፀናች ሀገር ገንብተናል።

በተለይ የውስጥና የውጭ ፈተናዎችን በጋራ በመከላከል በዕድገትና ብልጽግና ጎዳና ላይ የምትገኝ ሀገር ፈጥረናል ሲሉም ተናግረዋል።

አዲሱ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ከ32 በላይ ብሔር ብሔረሰቦችን በአንድ በማስተሳሰር በሀገር ደረጃ የብዝሃነት መገለጫና ተምሳሌት ነው ብለዋል።


 

በተለይ ብዝሃነቱ ሰፊውን የብሔር ብሔረሰቦች ቁጥር ከመያዝ ባለፈ የተለያዩ ሃይማኖቶች፣ ባህልና አመለካከቶች በነጻነት የሚንጸባረቅበት መሆኑን ጠቅሰዋል። 

የክልሉን ሰላምና እድገት ከማረጋገጥ ባለፈ ከነባር ክልሎች ጋር በልማትና በብልጽግና ተወዳዳሪ ለማድረግ የጋራ ርብርብ ማድረግ እንደሚገባ አስረድተዋል።

ለዚህም "ክልሉ ያሉትን የብዝሃነት ፀጋዎች ለእድገትና ዘላቂ ሰላምን ለማረጋገጥ ተግተን በጋራ መስራት አለብን" በማለትም መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል ።

ህብረ-ብሄራዊነት ውበት ከመሆን ባለፈ ሀገራችን እንዳትበተን አስሮና ገምዶ የያዘ ፀጋችን ነው ያሉት ደግሞ የጌዴኦ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ዶክተር ዝናቡ ወልዴ ናቸው።

የብሔር ብሔረሰቦች ቀን መከበሩ አንድነታችንን ለማጠናከርና የተለያዩ ልምድና ተሞክሮዎችን ለመለዋወጥ ፋይዳው የጎላ መሆኑንም ጠቅሰዋል።

የዲላ ከተማ ምክር ቤት ዋና አፈ-ጉባኤ ወይዘሮ ፈትለወርቅ በቀለ በበኩላቸው የብሔር ብሔረሰቦችን ቀንን ስናከብር የህዝቦችን አንድነትና ትስስር በማጠናከር ሊሆን ይገባል ብለዋል።

የዲላ ከተማ የበርካታ ብሔር-ብሔረሰቦች መገኛ መሆኑን ጠቅሰው "ይህም የብዝሃነታችንና የውበታችን ማሳያ ነው"  ብለዋል።

በዓሉን ስናከብር ሁላችንም በተሰማራንበት የስራ ዘርፍ ውጤት በማስመዝገብ የከተማችንን ልማትና ሰላም በማጽናት ሊሆን ይገባል ሲሉም ተናግረዋል።

በበዓሉ የክልልና የዞኑ የሥራ ሃላፊዎች፣ አባገዳዎች፣ የሃገር ሽማግሌዎችና የሃይማኖት መሪዎች እንዲሁም ከዞኑ ሁሉም አካባቢዎች የተወጣጡ የህብረተሰብ ክፍሎችና ወጣቶች ተሳትፈዋል።

መርሃ ግብሩም በደም ልገሳ፣ በጥያቄና መልስ ውድድርና በተለያዩ ዝግጅቶች  በድምቀት ተከብሯል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም