ኢትዮጵያና ቼክ ሪፐብሊክ የጋራ የኢኮኖሚ የትብብር ኮሚሽን ለማቋቋም ተስማምተዋል - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያና ቼክ ሪፐብሊክ የጋራ የኢኮኖሚ የትብብር ኮሚሽን ለማቋቋም ተስማምተዋል
አዲስ አበባ፤ ህዳር 19/2016(ኢዜአ)፦ኢትዮጵያና ቼክ ሪፐብሊክ የጋራ የኢኮኖሚ የትብብር ኮሚሽን ለማቋቋም ከስምምነት ላይ መድረሳቸው ተገለጸ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ከቼክ ሪፐብሊክ አቻቸው ፔትር ፊያላን ጋር ባደረጉት ውይይት በሁለቱ ሀገራት መካከል በተለያዩ ዘርፎች ያሉ ግንኙነቶችን ተግባራዊ ለማድረግ የሚያግዝ የጋራ የኢኮኖሚ የትብብር ኮሚሽን ለማቋቋም ከስምምነት ላይ ደርሰዋል።
የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዴኤታ ሰላማዊት ካሳ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድን(ዶ/ር) የቼክ ሪፐብሊክ ቆይታን አስመልክተው ማብራሪያ ሰጥተዋል።
በዚህም፤ በቱሪዝም በተለይ በቅርስ ጥበቃና ምርምር፣ በወታደራዊ፣ ግብርና አንዲሁም በኢኮኖሚ ዘርፎች ያለውን ትብብር ማጠናከር በሚቻልበት ሁኔታ ላይ መወያየታቸውን አንስተዋል።
ግንኙነቱን ለማጠናከር የሁለቱ ሀገራት የጋራ የኢኮኖሚ ትብብር ኮሚሽን ማቋቋም አስፈላጊ መሆኑ ከስምምነት ላይ መደረሱንና ይህም በመሪዎች ደረጃ ስምምነት የተደረሰባቸውን ጉዳዮች ወደ ተግባር ለማስገባት ወሳኝ መሆኑን አመላክተዋል።
በመንግስታቱ መካከል የተጀመረውን ግንኙነት ወደ ህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ለማሳደግ እንደሚያስፈልግና ይህንንም ከቱሪዝም ዘርፉ ጋር አብሮ ማሳደግ እንደሚቻል ማንሳታቸውን ገልጸዋል።
ለዚህም በፕራግ የኢትዮጵያን ታሪክ፣ ባህልና የቱሪዝም መዳረሻዎች የሚያስተዋውቅ ኤግዚቢሽን ለማቅረብ እንዲቻልና የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ፕራግ ቀጥታ በረራ እንዲጀምር ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጥያቄ አቅርበዋል ብለዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በቼክ ሁለተኛ መዳረሻቸው በሆነችው ቡሩኖ ከተማ ባደረጉት ጉብኝት ኢትዮጵያ ውስጥ የተለያዩ ስራዎችን እያከናወነ የሚገኘው ዜቶር የትራክተር አምራች ኩባንያን በንግዱ ዘርፍ ያለውን ግንኙነት ወደ መንግስት ደረጃ ከፍ በማድረግ ጥራት ያለው የግብርና ማሽነሪዎችን ለአርሶ አደሩ ተደራሽ ለማድረግ ብሎም የተሻለ የፋይናንስ አቅርቦት እንዲኖር ለማስቻል በሁለቱ መንግስታት መካከል አሁን የተመሰረተውን ጠንካራ ግንኙነት መጠቀም እንደሚቻል ማንሳታቸውን ገልጸዋል።
ይሄም በሀገር ደረጃ ለግብርናው ዘርፍ የተሰጠውን ትኩረት ለማሳካት ዘመናዊ የግብርና ማሽነሪዎች አስፈላጊ በመሆኑ ኩባንያው ያለውን ትልቅ አቅም በመጠቀምና ከመንግስት ጋር ትብብር በማድረግ ኢትዮጵያ ውስጥ ማምረቻ እንዲከፍት ጥሪ ማቅረባቸውን አንስተዋል።