ቀጥታ፡

የዋጋ ንረቱን ለመቀነስ የተወሰዱ የገንዘብ ፖሊሲ የማሻሻያ እርምጃዎች ውጤት እያስገኙ ነው

አዲስ አበባ ፤ ህዳር 19/2016(ኢዜአ):- የዋጋ ንረቱን ለመቀነስ የተወሰዱ የገንዘብ ፖሊሲ የማሻሻያ እርምጃዎች ተጨባጭ ውጤት እያስገኙ መሆኑን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገለጸ።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ ማሞ ምህረቱ የባንኩን የ2016 የሩብ ዓመቱን የሥራ አፈፃፀም ሪፖርት ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የፕላን በጀትና ፋይናንስ ቋሚ ኮሚቴ አቅርበዋል።

በሪፖርታቸውም፤ ተለዋዋጭ የተፈጥሮና ሰው ሰራሽ ችግሮች በዓለም ኢኮኖሚ ላይ ከፍተኛ መቀዛቀዝ መፍጠሩንና ይህም በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ላይ አሉታዊ ጫና ማሳደሩን አንስተዋል።

በሌላ በኩል ያደጉት አገራት ለታዳጊ አገራት ይሰጡት የነበረው ብድርና እርዳታ በከፍተኛ ሁኔታ መቀነሱን ጠቅሰው ይህም ኢትዮጵያን ጨምሮ በርካታ አገራት የዋጋ ንረት እንዲያጋጥማቸው አድርጓል ነው ያሉት።

ይሁንና የዋጋ ንረትን ለመቀነስ ብሔራዊ ባንክ የተለያዩ የገንዘብ ፖሊሲ ማሻሻያ እርምጃዎችን እየወሰደ መሆኑንም አንስተው ይህንን ተከትሎ ባንኩ የዋጋ ንረትን በዚሀ ዓመት ሰኔ መጨረሻ ከ20 በመቶ በታች የማውረድ እቅድ ይዞ እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

የአገር ውስጥ የብድር እድገት በ14 በመቶ ጣሪያ እንዲገደብ፣ መንግሥት ለበጀት ጉድለት ከብሔራዊ ባንክ የሚወስደውን የብድር መጠን በእጅጉ ለመቀነስና ባንኮችም የበጀት ጉድለታቸውን በራሳቸው እንዲሞሉ እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።

ይህንንም ተከትሎ ለወራት ከ30 በመቶ በላይ የነበረው የዋጋ ንረት በመስከረም ወር ወደ 27 ነጥብ 7 በመቶ ዝቅ ማለቱን ጠቁመዋል አሃዙ ይበልጥ ዝቅ ለማድረግ ትኩረት ተደርጓል ነው ያሉት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም