የጂንካ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ ችግር ፈቺና ፈርጀ ብዙ ቴክኖሎጂዎችን በማፍለቅ ለተጠቃሚዎች እያሻገረ ነው 

ጂንካ፤ ህዳር 19/2016 (ኢዜአ)፡- የጂንካ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ ውጤታማ፣ ችግር ፈቺና ፈርጀ ብዙ የሆኑ ቴክኖሎጂዎችን በማፍለቅ ለተጠቃሚዎች ለማሻገር አትኩሮ እየሰራ መሆኑን ገለጸ ።

ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረጉት የኮሌጁ ዲን አቶ ካሳሁን ጌታቸው እንዳሉት፤ ኮሌጁ ችግር ፈቺ የሆኑ ቴክኖሎጂዎችን በማፍለቅ ለማህበረሰቡ በማሸጋገር ተጠቃሚ ለማድረግ አልሞ እየሰራ ይገኛል። 

ኮሌጁ በአካባቢው የሚገኙ ያልተነኩ አቅሞችን ለመጠቀም የተጀመሩ ጥረቶችን ለማገዝ የማህበረሰቡን ድካም የሚቀንሱና ውጤታማነትን የሚያጎለብቱ ቴክኖሎጂዎች ማፍለቅና ማሸጋገር ላይ ዋናው ትኩረት አድርጎ እየተሰራ ይገኛል ብለዋል ።

በተለይ ኮሌጁ ''ኢትዮጵያ ታምርት'' በሚል መሪ ሀሳብ በተጀመረው አገራዊ ንቅናቄ በከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ወደ ሀገር ውስጥ የሚገቡ ማሽነሪዎችን በሀገር ውስጥ ምርቶች ለመተካት ባደረገው እንቅስቃሴ ውጤት እየተገኘ መሆኑን ጠቁመዋል።

ለአብነት በኮሌጁ ከተሰሩ የፈጠራ ስራዎች መካከል ከ30 እስከ 40 ሜትር ጥልቅ ጉድጓድ መቆፈር የሚያስችል ማሽን  መሰራቱን ያነሱት አቶ ካሳሁን ከውጭ ሲገባ ከሚጠይቀው ወጪ አንጻር እጅግ ዝቅተኛ በሆነ ዋጋ ለማህበረሰቡ እየቀረበ እንደሚገኝ ነው የተናገሩት።

ኮሌጁ የአርሶ አደሮችን ድካም ለማቃለል ከፈጠራቸው ችግር ፈቺ ቴክኖሎጂዎች መካከል የበቆሎ መፈልፈያ፣ የገብስና የጥራጥሬ መፈተጊያ ማሽኖች ይገኙበታል።

የገብስና የጥራጥሬ  መፈተጊያ ማሽኑም  በባህላዊ መንገድ ጤፍ፣ ማሽላና ሌሎች ሰብሎችን በመውቃት የሚገጥመውን የምርት ብክነት መቀነስ የሚያስችል ቴክኖሎጂ መሆኑን አመላክተዋል።


 

በኮሌጁ የቴክኖሎጂ ሽግግርና የኢንዱስትሪ ኤክስቴንሽን ባለሙያ አቶ እስጢፋኖስ እያሱ በኮሌጁ የፈለቁ ማሽኖች የኃይል አማራጭ ስላላቸው  መብራት በሌለባቸው አካባቢዎች በነዳጅ የሚሰሩ መሆናቸውን ገልጸዋል።

ይህም ከኃይል አቅርቦት ጋር የሚስተዋሉ ችግሮችን መቅረፍ የሚያስችል ችግር ፈቺ ቴክኖሎጂ ነው ያሉት።

ማሽኑ የኃይል አማራጭ እንዲኖረው መደረጉ አርሶ አደሮች እና በግብርና ላይ የተሰማሩ ኢንቬስተሮች ማሽኑን በተለያየ ቦታ በማንቀሳቀስ መጠቀም እንዲችሉ ታስቦ እንደተሰራም አስረድተዋል።

በተለይ ተቋሙ የፈጠረው የጥራጥሬ መፈተጊያ ማሽን ስንዴ፣ ገብስ፣ ማሽላ እና ሩዝ መፈተግ የሚያስችል መሆኑን ጠቅሰዋል። 

ይህም የአርሶ አደሩን ጊዜና ጉልበት ከመቆጠቡም ባሻገር የምርት ብክነትን ያስቀራል ብለዋል።

በገጠር አካባቢዎች በስፋት የሸክላ ሥራ የሚተገበርና አሰራሩም ሁዋላ ቀር በመሆኑ ከዘርፉ የሚገኘው ኢኮኖሚያዊ ጥቅም አነስተኛ መሆኑን የገለፁት አቶ እስጢፋኖስ፤ ስራው በሰው ጉልበት  በመሰራቱ እጅግ አድካሚ እንደሆነም አንስተዋል።

ኮሌጁ ይህን ችግር በማየት የሸክላ አፈር መፍጨት፣ ማቡካትና የተለያዩ ቅርፆችን እንዲይዝ የሚያደርግ ዘመናዊ የሸክላ መስሪያ ማሽን መስራት ችሏል ብለዋል።

ኮሌጁ  የእርሻ ስራውን ለማዘመን እና የከብት እርባታውን አዋጭ ለማድረግ ከሚያግዙ ቴክኖሎጂዎች መካከል አነስተኛ የእርሻ ትራክተር እና የወተት መናጫ ማሽን እና ሌሎችንም ማፍለቅ መቻሉንም ገልጸዋል ።


 

በፈጠራ ስራዎች ላይ ከተሳተፉ የኮሌጁ ተማሪዎች መካከል ተማሪ ሙሉቀን አለማየሁ ለኢዜአ እንደገለፀው በኮሌጁ 30 በመቶ የንድፈ ሃሳብ፣ 70 በመቶ የሚሆነውን ደግሞ በተግባር ልምምድ እንደተማሩ ተናግሯል።

የጂንካ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ በአሁኑ ወቅት በግብርና፣ በማኑፋክቸሪንግ፣ በኮንስትራክሽን እና በሌሎች ተዛማጅ የትምህርት መስኮች 501 ነባር ተማሪዎችን እያሰለጠነ ሲሆን ለ2016 ዓ.ም የትምህርት ዘመን ደግሞ 600 ተማሪዎችን ተቀብሎ ለማስተማር በዝግጅት ላይ ይገኛል።

ከመደበኛ የመማር ማስተማር ሰራው ጎን ለጎን 1 ሺህ ለሚሆኑ ሰልጣኞች በገበያ አዋጭነትና ስራ ፈጠራ ላይ አጫጭር ስልጠናዎችን ለመስጠት መዘጋጀቱንም ከኮሌጁ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም