በኢትዮጵያ የካፒታል ገበያ ለመሳተፍ አምስት የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ዝግጅት እያደረጉ ነው 

117

አዲስ አበባ ፤ህዳር 19/2016 (ኢዜአ):-በኢትዮጵያ የአገር ውስጥና የውጭ ድርጅቶች ለመሳተፍ ከፍተኛ ፍላጎት ባሳዩበት የካፒታል ገበያ ቀዳሚ የሆኑ አምስት የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ተለይተው ዝግጅት እያደረጉ መሆኑ ተገለጸ። 

የካፒታል ገበያውን በተያዘው ዓመት ለማስጀመር የሚያስችል አብዛኛው ሥራ መጠናቀቁም ተገልጿል።

ኢትዮጵያም ባደጉት አገራት በስፋት እየተተገበረ ያለውን የካፒታል ገበያን ወደ ሥራ ለማስገባት አዋጅ 1248/2013 አፀድቃ ወደ ሥራ ለመግባት እንቅስቃሴ ጀምራለች።

የካፒታል ገበያ የኢትዮጵያን ማክሮ ኢኮኖሚ ሚዛን በማስተካከል የጎላ ሚና እንደሚኖረውና ለግልም ሆነ ለድርጅቶች በቂ የሥራ ማንቀሳቀሻ ገንዘብ ለማስገኘት እንደሚያግዝ ይገለጻል።

በተጨማሪም የኢትዮጵያ ምጣኔ ኃብት በማይዋዥቅ መልኩ በዘላቂነት እንዲያድግ የፋይናንስ አገልግሎት ዘርፉን አስቻይ ሁኔታ ለማስፋትና ቁጠባን ለማበረታታት ከፍተኛ ጠቀሜታ እንዳለው ይነገራል። 

በኢትዮጵያም አዋጁ ከፀደቀ በኋላ የካፒታል ገበያውን ለመጀመር የሚያስችል  የተለያዩ እንቅስቃሴዎች  በመደረግ ላይ መሆኑ ይታወቃል።

እንቅስቃሴውን አስመልክቶ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት የኢትዮጵያ የካፒታል ገበያ ባለሥልጣን ከፍተኛ የሕግ አማካሪ ሰለሞን ዘውዴን አነጋግሯል።

አቶ ሰለሞን እንዳሉትም በኢትዮጵያ በርካታ የውጭና የአገር ውስጥ ባለሃብቶች በገበያው ለመሳተፍ ከፍተኛ ፍላጎት በማሳየት ላይ ናቸው።

ከፍተኛ ፍላጎት የታየበት የካፒታል ገበያ ለማስጀመር የሚያስችል የመጨረሻ ምዕራፍ ዝግጅት እየተደረገም እንደሆነም ተናግረዋል።

አሁን ላይ አምስት የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ወደ ገበያው ለመግባት ዝግጅት እያደረጉ ሲሆን የኬንያ፣ የናይጄሪያና የደቡብ አፍሪካ ኩባንያዎችም በካፒታል ገበያው ለመሳተፍ ፍላጎት ማሳየታቸውን አንስተዋል። 

የተለዩ የመንግሥት የልማት ድርጅቶችም ይሁን  ፍላጎት ያሳዩ የውጭ ኩባንያዎች አጠቃላይ የዝግጅት ሥራዎች ሲጠናቀቁ ወደ ሥራ እንደሚገቡ ገልፀዋል።

አሁን ላይ የመመሪያ ማዘጋጀት፣ የግንዛቤ መስጨበጫና የተሳታፊ ድርጅቶች ልየታ ሥራ እየተከናወነ ሲሆን፤ ወደ ካፒታል ገበያው የሚገባውን  ድርጅት ግለሰብና ባለሃብት ማስተዳደር የሚችል የሕግ ማዕቀፍ ተዘጋጅቶ በቅርቡ ወደ ሥራ ለማስገባት እየተሰራ ነው ብለዋል።

የካፒታል ገበያው  አከናዋኝ፣ የኢንቨስትመንት ባንክ፣ የውክልና አስተዳዳሪዎች፣ የጋራ ኢንቨስትመንት ባንክ ሥራ አስኪያጅን ጨምሮ በካፒታል ገበያው አገልግሎት ለሚሰጡ 15 ዘርፎችም ፈቃድ መስጠት የሚያስችሉ መመሪያዎች መዘጋጀታቸውንም ነው የተናገሩት።

በተያዘው ዓመት የቅድመ ዝግጅት ሥራዎችን አጠናቆ የካፒታል ገበያን ወደ ሥራ ለማስገባት እየተሰራ መሆኑንም ጠቁመዋል። 

የካፒታል ገበያው በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንትና ቁጠባን ከማሳደጉ ባሻገር የዲጂታል ግብይትን በማፋጠን በኩል ሰፊ አስተዋጽዖ እንደሚኖረውም ጠቁመዋል።

ለኢንቨስተሮች ሥጋቶችን የሚቀንስ፣ ለኩባንያዎችና ገንዘብ ለሚያስፈልጋቸው ደግሞ ተጨማሪ የፋይናንስ ጥቅም እንዲያገኙ ወይም የባንክ ብድር ዓይነት ድጋፍ እንዲያገኙ እንደሚያደርግ እንዲሁ።  

አዳዲስ የሥራ ዕድሎች እንዲፈጠሩ እንደሚያደርግም ነው የተናገሩት።

የካፒታል ማርኬት ተሳታፊ የሚባሉ ደላሎች፣ ነጋዴዎች፣ የኢንቨስትመንት ባንኮች፣ ሌሎች የፈንዱን ፍሰት የሚያግዙ ተዋንያን ናቸው። 

ለአገሪቱ የኢኮኖሚ እድገት ለማንቀሳቀስ ከፍተኛ ጥቅም እንዳለው የሚታመንበት የካፒታል ገበያ እውን እንዲሆን ሁሉም የበኩሉን መወጣት እንዳለበት አብራርተዋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም