በምስራቅ ሸዋ ዞን 121 ሺህ ሄክታር መሬት በበጋ መስኖ ስንዴ ለምቷል

151

አዳማ፤ህዳር 19/2016 (ኢዜአ)፦ በምስራቅ ሸዋ ዞን 121 ሺህ ሄክታር መሬት በኩታገጠም በበጋ መስኖ ስንዴ መልማቱን የዞኑ ግብርና ጽሕፈት ቤት ገለፀ።

የምስራቅ ሸዋ ዞን ግብርና ጽሕፈት ቤት ምክትል ሃላፊ አቶ አብነት ዘገየ ለኢዜአ እንደገለፁት በዞኑ በዘንድሮው የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት 350 ሺህ ሄክታር ለማልማት ታቅዶ ስራው ተጀምሯል።

በእስከ አሁኑ ሂደት 192 ሺህ ሄክታር መሬት መታረሱን የገለፁት አቶ አብነት፤ እስከ ትናንት ድረስ 121 ሺህ ሄክታር መሬት በኩታ ገጠም ታርሶ በዘር መሸፈኑን ተናግረዋል።

የበጋ መስኖ ስንዴ ልማቱን 95 በመቶ የሚሆነውን በሜካናይዜሽንና በኩታ ገጠም ለማልማት ታቅዶ ወደ ስራ እንደተገባም ገልጸዋል።


 

በዚህም እስከ አሁን በዘር የተሸፈነው 121 ሺህ ሄክታር በሜከናይዜሽንና በኩታ ገጠም መልማቱን አመልክተዋል።

ምክትል ሃላፊው በዘንድሮው የበጋ መስኖ ስንዴ ከዞኑ 14 ነጥብ 4 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለማግኘት መታቀዱን ተናግረዋል።

ከግብዓት አቅርቦት አንጻርም ለዘንድሮው የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት 350 ሺህ ኩንታል የአፈር ማዳበሪያና ምርጥ ዘር መቅረቡን ገልጸዋል።

በዞኑ የአደኣ ወረዳ ግብርና ጽሕፈት ቤት ሃላፊ አቶ ሮቢ ያዴሳ በበኩላቸው በወረዳው 2 ሺህ ሄክታር መሬት በበጋ መስኖ ስንዴ የማልማት ስራ ላይ መሆናቸውን ተናግረዋል። 

በዚህም ለአርሶ አደሩ የስንዴ ምርጥ ዘር፣ የአፈር ማዳበሪያና የእርሻ ትራክተር በተመጣጣኝ ዋጋ እየቀረበ መሆኑንም ጠቁመዋል።


 

በወረዳው በመስኖ ስንዴ ልማት ከተሰማሩ አርሶ አደሮች መካከል አቶ ከተማ ሽፈራው ከአካባቢው አርሶ አደር ጋር በመሆን በኩታ ገጠም በ4 ሄክታር መሬት ላይ ስንዴ እያለሙ መሆኑን ተናግረዋል።

'በዋናነት የአካባቢው አርሶ አደሮች ለስንዴ ልማቱ በራሳቸው በባለሙያ ታግዘው ያለሙትን ምርጥ ዘር በመጠቀም በሜካናይዜሽን እያለሙ መሆናቸውንም አክለዋል።

አርሶ አደር መኮንን ሽብሩ በበኩላቸው በግማሽ ሄክታር መሬት ላይ የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት እያከናወኑ መሆኑን ጠቅሰዋል።

በዘንድሮው በጋ በሜካናይዜሽንና ኩታ ገጠም በማልማታቸው የተሻለ ምርት እንደሚያገኙ ተስፋ መሰነቃቸውንም አስረድተዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም