የአማራ ክልል ከፍተኛ አመራሮች በክልሉ ወቅታዊ ሁኔታ ላይ ውይይት እያካሄዱ ነው

አዲስ አበባ ፤ህዳር 19/2016 (ኢዜአ):- የአማራ ክልል ከፍተኛ አመራሮች በክልሉ ወቅታዊ ሁኔታ ላይ ውይይት እያካሄዱ ይገኛል።

በመድረኩ ላይ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አረጋ ከበደ ባስተላለፉት መልእክት በክልሉ በተፈጠረው ግጭት እና አለመረጋጋት የተነሳ ከወትሮው በተለይ ሁኔታ መከናወን ያለባቸው የልማት ስራዎች መስተጓጎላቸውን ጠቁመዋል።


 

በመከላከያ ሠራዊትና በክልሉ የፀጥታ ኃይል፣ አጠቃላይ አመራሩና ሰላም ወዳዱ ህዝብ በቅንጅት በሰሩት ስራ አብዛኛው የክልሉ አካባቢዎች አንፃራዊ ሰላም ሰፍኗል ብለዋል።

የክልሉን ሰላም ለማረጋገጥና ወደ ልማት ስራዎች ለመመለስ ባለን ጽኑ ፍላጎት በተከታታይ የግንዛቤ ማሳደግ ስራዎች መስራታችንም አሁን ለተገኘው አንጻራዊ ሰላም ከፍተኛ አስተዋፅዖ አበርክቷል ሲሉ ርዕሰ መስተዳድሩ ገልጸዋል።

የተገኘውን አንጻራዊ ሰላም ለማጽናት ይቻል ዘንድ ወቅቱን እና ሁኔታዎችን ያገናዘበ የጋራ አመራር የመስጠትና የማረጋገጥ ተግባር ከመላው አመራር እንደሚጠበቅ የጠቆሙት ርዕሰ መስተዳድሩ ህዝቡ ካለበት ችግር ውስጥ በፍጥነት ለማውጣት ከወትሮው የተለየ ስራ ይጠይቃል ብለዋል።

ከሰሞኑ ከህዝቡ ጋር በተደረጉ የውይይት መድረኮች የተገኙ ገንቢ እና ተራማጅ ሀሳቦችን በተጨባጭ ወደ ተግባር በመቀየር የክልሉን የሰላም፣ የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ምላሽ መስጠት ይኖርብናል ነው ያሉት።

ድክመቶች ሳይደገሙ በአዲስ መታደስና ታሪክ መጻፍ እንደሚገባም መግባባት ላይ መደረሱን ከክልሉ ኮሚኒኬሽን ቢሮ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም