የ5-ጂ ሞባይል ኔትዎርክ መስፋፋት የዲጂታል ልማትን ከማፋጠን ባለፈ ሀገራዊ የምጣኔ ኃብት እድገትን ለማረጋገጥ ሚናው የላቀ ነው

አዲስ አበባ ፤ህዳር 19/2016 (ኢዜአ):- በኢትዮጵያ የአምስተኛው ትውልድ (5-ጂ) የሞባይል ኔትዎርክ አገልግሎት መስፋፋት የዲጂታል ልማትን ከማፋጠን ባለፈ ሀገራዊ የምጣኔ ኃብት እድገትን ለማረጋገጥ ሚናው የላቀ መሆኑን የኢትዮ-ቴሌኮም ዋና ሥራ አስፈጻሚ ፍሬህይወት ታምሩ ገለጹ።

ኢትዮ-ቴሌኮም የአምስተኛውን ትውልድ (5-ጂ) የሞባይል ኔትዎርክ በጅግጅጋ ከተማ በይፋ አስጀምሯል።

የኢትዮ-ቴሌኮም ዋና ሥራ አስፈጻሚ ፍሬህይወት ታምሩ፤ በማስጀመሪያ ሥነ-ሥርዓቱ ላይ ባስተላለፉት መልዕክት በዓለም ላይ እጅግ ፈጣን የሚባለውን የአምስተኛው ትውልድ (5-ጂ) የሞባይል ኔትዎርክ ኢትዮጵያ መጠቀም ጀምራለች ብለዋል።

የአምስተኛው ትውልድ (5-ጂ) ኔትዎርክ ተጠቃሚ ከሆኑ  የዓለም አገራት መካከል ኢትዮጵያ አንዷ መሆኗንም ጠቅሰዋል።

የ5-ጂ ኔትዎርክ ቀደም ሲል በአዲስ አበባ እና አዳማ በይፋ መጀመሩን አስታውሰው፤ አሁን ላይ በሱማሌ ክልል ጅግጅጋ ከተማ በመጀመሩ እንኳን ደስ ያላችሁ ብለዋል።

በኢትዮጵያ የማስፋፋት ሥራው በልዩ ትኩረት እየተከናወነ መሆኑን ጠቅሰው፤ በቀጣይም ተጠናከሮ ይቀጥላል ሲሉ ተናግረዋል።

የአምስተኛው ትውልድ (5-ጂ) የሞባይል ኔትዎርክ አገልግሎት የማስፋፋት ሥራ ለዲጂታል ኢትዮጵያ እውን መሆን የላቀ አስተዋጽዖ እንዳለውም ገልፀዋል።

የ5-ጂ ኔትዎርክ አገልግሎት በጅግጅጋ ከተማ መጀመሩም የንግድና የመረጃ ሥርዓቱን ለማሳለጥና የመንግሥትን አገልግሎት አሰጣጥ የሚያቀላጥፍ መሆኑን ጠቅሰዋል።


 

የሱማሌ ክልል ምክትል ርዕሰ-መስተዳድር ኢብራሂም ኡስማን፤ የቴክኖሎጂው እውን መሆን በክልሉ ለተጀመሩ የልማት ሥራዎች መፋጠን እንዲሁም በተለያዩ ሴክተሮች ቀልጣፋ አገልግሎት ለመስጠት የሚያግዝ መሆኑን ገልፀዋል።

በጅግጅጋ ኢዜአ ካነጋገራቸው የከተማዋ ነዋሪዎች መካከል ወይዘሮ ራሁ ጠይብካስ እና አብዱረዛቅ ሐሰን

የአምስተኛው ትውልድ (5-ጂ) የሞባይል ኔትዎርክ አገልግሎት መጀመር በንግዱም ይሁን በሌሎች አገልግሎቶች ተጠቃሚ የሚያደርግ በመሆኑ ተደስተናል ብለዋል።

የ5-ጂ የኔትዎርክ አገልግሎት በተለይም ለስማርት ሲቲ፣ ስማርት ትራንስፖርት፣ የትምህርት ሥርዓት፣ ለጤና፣ ለውሃ፣ የግብርና ልማት፣ ለንግድና የፋይናንስ ሴክተር፣ ለኢንዱስትሪ፣ ለስማርት የመንግሥት አስተዳደር እና ሌሎችም ሴክተሮች የላቀ አበርክቶ እንዳለው ይነገራል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም