ከአንድ ሚሊየን ኩንታል በላይ የአፈር ማዳበሪያ ወደ አገር ውስጥ ገብቷል 

145

አዲስ አበባ ፤ ህዳር 19/2016 (ኢዜአ)፡- ለ2016/17 የምርት ዘመን ለመግዛት ከታቀደ 23 ሚሊየን ኩንታል በላይ የአፈር ማዳበሪያ እስከ አሁን ከአንድ ሚሊየን ኩንታል በላይ የአፈር ማዳበሪያ ወደ አገር ውስጥ መግባቱን የግብርና ሚኒስቴር ገለጸ። 

የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ሶፊያ ካሳ ዛሬ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ፤ በምርት ዘመኑ ከ23 ነጥብ 3 ሚሊየን ኩንታል በላይ የአፈር ማዳበሪያ ለመግዛት ታቅዷል።

እስካሁን 14 ነጥብ 79 ሚሊየን ኩንታል ኤን ፒ ኤስ ዝርያና ዩሪያ የአፈር ማዳበሪያ ግዥ መፈጸሙን ጠቁመው ከተገዛው ውስጥ ከአንድ ሚሊየን ኩንታል በላይ የአፈር ማዳበሪያ ወደ አገር ውስጥ መጓጓዙን ገልጸዋል። 

እስከ ታህሳስ ወር መጀመሪያ አካባቢ ተጨማሪ 1 ነጥብ 7 ሚሊየን ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ጂቡቲ እንደሚደርስ ጠቁመው በዚህ ዓመት የአፈር ማዳበሪያ በፍጥነት ወደ አገር ውስጥ እየገባ እንደሚገኝ ተናግረዋል። 

መንግሥት የዓለም ከፍተኛ የማዳበሪያ ጭማሪና የአርሶ አደሩን የመግዛት አቅም ከግምት በማስገባት ከፍተኛ ድጎማ ሲያደርግ መቆየቱን ጠቅሰው ባለፉት ሦስት ዓመታት የ52 ቢሊየን ብር ድጎማ ማድረጉን ተናግረዋል። 

በዚህም ምርትና ምርታማነት ለማሳደግ ከዚህ በፊት ከነበረው አሰራር በማሻሻል የአፈር ማዳበሪያ በፍጥነት እንዲገባ መደረጉን ጠቁመዋል።

የአፈር ማዳበሪያውን በተቀናጀ ሁኔታ ወደ አገር የማጓጓዝ ሥራ በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።  

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም