በኢንዱስትሪ ፓርኮችና በድሬዳዋ ነፃ ንግድ ቀጠና ውስጥ የሚገኙ የኢንቨስትመንት አማራጮች ለፈረንሳይ አምራች ተቋማት ቀረቡ 

 አዲስ አበባ ፤ኀዳር 19 / 2016 (ኢዜአ):-በኢንዱስትሪ ፓርኮችና በድሬዳዋ ነፃ ንግድ ቀጠና ውስጥ የሚገኙ የኢንቨስትመንት አማራጮች ለፈረንሳይ አምራች ተቋማት መቅረባቸው ተገለጸ። 

በኢትዮጵያ ዘርፈ ብዙ ኢንቨስትመንቶች ላይ ለመሰማራት ፍላጎት ላላቸው የፈረንሳይ  አምራች ኩባንያዎችና ባለሀብቶች በኢትዮጵያ  ኢንዱስትሪ ፓርኮች እንዲሁም በድሬዳዋ ነፃ ንግድ ቀጠና ያሉ ምቹ የኢንቨስትመንት አማራጮች ቀርበዋል። 

የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ዋና ስራ አስፈፃሚ አክሊሉ ታደሰ እና የኢንቨስትመንት ምክትል ኮሚሽነር ተመስገን ጥላሁን አማራጮቹ ላይ ማብራሪያ ሰጥተዋል። 

የኮርፖሬሽኑ ዋና ስራ አስፈፃሚ አክሊሉ ታደሰ ኮርፖሬኑ በሚያስተዳድራቸው የኢንቨስትመንት ማዕከሎች በርካታ አዋጭና ምቹ አማራጮች መኖራቸውን ጠቁመው በዋናነትም በድሬዳዋ ነፃ ንግድ ቀጠና የንግድና የሎጂስቲክ ዘርፍ እንዲሁም በባህርዳርና ጅማ በአግሮ ፕሮሰሲንግ ዘርፍ ያልተነኩ እምቅ እድሎች እንዳሉ አሳውቀዋል። 

ዋና ስራ አስፈፃሚው አክለውም በቦሌ ለሚ ኢንዱስትሪ ፓርክ በአግሮፕሮሰሲግ ዘርፍ የተሰማራው ግዙፉ የፈረንሳይ የብቅል አምራች ኩባንያ ሱፍሌ ኢትዮጵያ በውጪ ምንዛሪ ታስገባው የነበረውን ምርት ሙሉ በሙሉ በማስቀረት በኩል ሚናው ከፍተኛ እንደሆነ ተናግረዋል።

ድርጅቱ ከ50 ሺ በላይ ለሚሆኑ አርሶ አደሮች የገበያ ትስስር መፍጠሩን በማስታወስ ኮርፖሬሽኑ በፓርኮቹ በተለያዩ የኢንቨስትመንት አማራጮች ለመሰማራት ፍላጎቱ ላላቸው አዳዲስ ኩባንያዎች አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ አረጋግጠዋል። 

በመድረኩ በኢንዱስትሪ ፓርኮች የሚገኙ የኢንቨስትመንት አማራጮችን ፤ የተገነቡና ለአምራቾች የቀረቡ አስቻይ መሰረተ ልማቶችን ፤ ምቹ የኢንቨስትመንት ፖሊሲዎችንና ማበረታቻዎችን እንዲሁም መሰል ዝርዝር ኢንቨስትመንት ተኮር ጉዳዮችን የተመለከተ ዝርዝር ሰነድ ቀርቦ ማብራሪያ ተሰጥቶበታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም