ኢትዮጵያን ከመድኃኒት እና የህክምና ግብዓቶች ጥገኝነት ለማላቀቅ የአገር ውስጥ አምራቾችን መደገፍ ይገባል

አዲስ አበባ፤  ህዳር 19/2016 (ኢዜአ) የመድኃኒት እና የህክምና ግብዓቶች ፍላጎትን ለማሟላትና የውጪ ጫናን ለመቀነስ ለአገር ውስጥ አምራቾች  ድጋፍ ማድረግ እንደሚገባ ተጠቆመ፡፡

የጤና፣ ማህበራዊ ልማት፣ ባህልና ስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ከዘርፉ አጋር አካላት ጋር በመሆን በቅሊንጦ ኢንዱስትሪ ፓርክ በሚገኙ የመድኃኒት እና የህክምና ግብዓት አምራቾችን የመስክ ምልከታ አድርጓል።

በመስክ ምልከታው ላይ ጤና ሚኒስትርን ጨምሮ የምግብና መድኀኒት ቁጥጥር ባለስልጣን እና ሌሎች አጋር አካላት ተሳትፈዋል።

በኢንዱስትሪ ፓርኩ የሚገኙ ሶስት የመድኃኒትና የህክምና ግብዓት አምራቾች የተጎበኙ ሲሆን፣ አሁን የሚገኙበትን ደረጃና በዘርፉ ያሉባቸውን ተግዳሮቶች ለቋሚ ኮሚቴው አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ መድኃኒትና ህክምና ግብዓት አምራቾች ማህበር ፕሬዘዳንት ዶ/ር ዳንኤል ዋቅቶላ የአገር ውስጥ አምራቾች የአገር ውስጥ ፍላጎትን ከሟሟላት ባሻገር ኢትዮጵያን በዘርፉ ቀዳሚ ለማድረግ ከግሉ ዘርፍ ከፍተኛ ፍላጎት መኖሩን ለኮሚቴው አባላት ገልጸዋል።

አያይዘውም በፓርኮች የመሠረተ-ልማት አለመሟላትና የአገልግሎት ውድነት፣ ለመድኃኒት ማምረት ጥቅም ላይ የሚውሉ ግብዓቶች የታክስ ጫና፣ የመንግሥት የግዢ ሥርዓት የአገር ውስጥ አምራቾችን የሚያበረታታ አለመሆኑ በምንፈልገው ልክ እንዳንሰራ አድርጎናል ብለዋል።

ጠንካራ የውጪ ጫናዎችን የሚቋቋም የጤና ሥርዓት ለመገንባት መንግሥት የገበያ ዕድሎችን ከማመቻቸት ጀምሮ ለዘርፉ ተገቢውን ትኩረት ሊሰጥ እንደሚገባ ለቋሚ ኮሚቴው አስገንዝበዋል።

የቅሊንጦ ኢንዱስትሪ ፓርክ በበኩሉ 187 አልሚዎች ለመቀበል የሚያስችል አቅም እንዳለው የገለፀ ሲሆን ከ200 ሜጋ ዋት በላይ የኤሌክትሪክ ኃይል፣ የውሃ፣ የአንድ ማእከል አገልግሎት በማቅረብ ላይ እንደሚገኝ አስታውቋል፡፡


 

የጤና ማህበራዊ ልማት፣ ባህልና ስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ወ/ሮ ወርቀሰሙ ማሞ ባስተላለፉት መልዕክት አምራቾች እያደረጉት ያለው ጥረት አስደሳችና ሊበረታታ የሚገባው መሆኑን ገልፀዋል።

የውጪ ምንዛሬ እና የጉምሩክ እንዲሁም የፖሊሲ ችግሮችን ለመቅረፍ የጤናው ዘርፍ ተገቢውን ትኩረትና ድጋፍ ሊያደርግ እንደሚገባ ጠቁመዋል።

ልዩነቶችን ሁለቱንም ወገን ተጠቃሚ በሚያደርግ መልኩ በውይይት ለመፍታት ቋሚ ኮሚቴው እንደሚሰራ ገልጸዋል።

የጤና ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ፍሬሕይወት አበበ በበኩላቸው መስሪያ ቤታቸው በ2016 ዓ.ም ከ97 በላይ በሚሆኑ ምርቶች ላይ የአገር ውስጥ አምራቾች ብቻ በአቅርቦት እንዲሳተፉ መደረጉን ገልፀው፤ የአገር ውስጥ ምርት ጉዳይ ኢትዮጵያን ከውጪ ጥገኝነት ማለቀቅ በመሆኑ አብረን እንሰራለን ብለዋል።

የኢንዱስትሪና የማዕድን ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባላትም በመስክ ምልከታው ላይ መሳተፋቸውን ከህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም