አምባሳደር ሽፈራው ገነቲ በዜጋ ዲፕሎማሲ ዙሪያ ከባህሬን  ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የቆንስላ እና አስተዳደራዊ ጉዳዮች ረዳት ሚኒስትር   አምባሳደር ዶ/ር መሀመድ አሊ ባሀዛድ ጋር ተወያዩ

124

አዲስ አበባ ፤ህዳር 19 / 2016 (ኢዜአ):- በባህሬን የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ቆንስል ጄኔራል  አምባሳደር ሽፈራው ገነቲ ከባህሬን ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር   የቆንስላ እና አስተዳደራዊ ጉዳዮች ረዳት ሚኒስትር አምባሳደር ዶ/ር መሀመድ አሊ ባሀዛድ ጋር በዜጎች ጉዳይ እና ባህሬን በኢትዮጵያ የውክልና አድማስ እንዲኖራት በሚቻልበት መንገድ ላይ ተወያዩ። 


ኢትዮጵያ ከዚህ በፊት  የባህሬንን የሥራ ስምሪት ህግን በተቃረነ መልኩ የታዩ የተወሰኑ እንቅስቃሴዎችን ቆንስላ ጄኔራል ጽህፈት  ቤቱ  ማስተካከያ ማድረጉን ገልፀዋል።

አሁን ላይ የዜጎች ጉዳይ በቆንስላ ጄኔራል ጽህፈትቤቱ ባለሙያዎች ብቻ እየተሰራ መሆኑን አምባሳደር ሽፈራው  በውይይቱ አንስተዋል ። 


 

በህገወጥ መንገድ ያለመኖሪያ ፍቃድ የሚኖሩ ዜጎች  የመኖሪያ ፍቃድ አግኝተው  የሚሰሩበትን ሁኔታ እንዲመቻችና  በህገወጥ መንገድ በእየቤቱ እየዞሩ ገንዘብ የሚመነዝሩላቸውንም  ለማስቀረት  የባህሬን መንግስት አስፈላጊውን ድጋፍ እንዲያደርግ ጠይቀዋል።   


በሁለቱ አገራት መካከል ያለውን የሁለትዮሽ ግንኙነት በማሳደግ  በሰራተኛ ስምሪት፣ የንግድና ቱሪዝም ዘርፍ ትብብርን ማጠናከር  እንዲሁም  አዲስ አበባ የአፍሪካ ህብረትና የብዙ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች መቀመጫ በመሆኗ የባህሬን ንጉሳዊ መንግስት ውክልና እንዲኖረው ጠይቀዋል። 


ረዳት ሚኒስትሩ አምባሳደር ዶ/ር መሀመድ አሊ ባሀዛድ በበኩላቸው ከኢትዮጵያዊያን ዜጎች ጋር በተያያዘ ሲስተዋሉ የነበሩ ችግሮች መኖራቸውን በማስታወስ፣ ችግሮቹን ለመቅረፍ ቆንስል ጄኔራል ጽህፈት ቤቱ በኩል የተወሰዱትን እርምጃዎችን  አድንቀዋል። 

ባህሬን በቀጣይ በአዲስ አበባ ኤምባሲ ለመክፈት የሚያስችል ጥናት የምታደርግ መሆኗን ገልፀዋል።

ጥናቱ አልቆ ወደ ሥራ እስከሚገባ የክብር ቆንስላ ህጉን ተከትሎ እንደምትሰይም መናገራቸውን  ከውጭ ጉዳይ ሚስቴር ማህበራዊ ገጽ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም