የትምህርት ሚኒስቴር 10 ነጥብ 6 ሚሊየን መጽሐፍቶችን ለክልሎች አሠራጨ

አዲስ አበባ ፤ ህዳር 18/2016 (ኢዜአ)፡- የትምህርት ሚኒስቴር ካሳተመው 20 ነጥብ 6 ሚሊየን የመማሪያ መጽሐፍት መካከል 10 ነጥብ 6 ሚሊየን የሚሆኑት ለክልሎች መሠራጨታቸውን ገለፀ።   

32ኛው የትምህርት ጉባዔ በሶማሌ ክልል በጅግጅጋ ከተማ እየተካሄደ ነው።


  

በትምህርት ሚኒስቴር በስትራቴጂክ ጉዳዮች ሥራ አስፈጻሚ የዕቅድና በጀት ዝግጅትና  ክትትል ግምገማ ቡድን መሪ እሸቱ ገላዬ፤ "የትምህርት ዘርፍ ሪፎርም ሥራዎች አፈጻጸም" በተመለከተ ለጉባዔው ሪፖርት አቅርበዋል።         

የአዲሱ ሥርዓተ-ትምህርት ፖሊሲ ተግባራዊ ለማድረግ የመጽሐፍት አቅርቦት ተግዳሮቶችን ለመፍታትም የትምህርት ሚኒስቴር የሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎችን መጽሐፍት እንዲሁም ክልሎች የአንደኛ ደረጃ ተማሪዎችን መጽሐፍት እንዲያሳትሙ መግባባት ላይ መደረሱን ገልፀዋል።   

በዚህም በተያዘው በጀት ዓመት የትምህርት ሚኒስቴር 20 ነጥብ 6 ሚሊየን መጽሐፍትን ማሳተሙን ገልጸው፤ ከዚህ ውስጥ 10 ነጥብ 6 ሚሊየኑ ወደ አገር ውስጥ ገብቶ ለክልሎች መከፋፈሉን ተናግረዋል። 

ቀሪዎቹ 10 ሚሊየን መጽሐፍትም ከጅቡቲ ወደብ ወደ አገር ውስጥ በመጓጓዝ ላይ መሆኑን ጠቁመዋል።

በበጀት ዓመቱ ከመንግሥትና ከኅብረተሰቡ 22 ቢሊየን ብር በማሰባሰብ በመጀመሪያው ሩብ ዓመት ከ 2 ነጥብ 7 ሚሊየን በላይ ከቅድመ አንደኛ እስከ 8ኛ ክፍል ተማሪዎችን በትምህርት ቤት ምገባ ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን ጠቁመዋል።    

የትምህርት ቤቶችን ደረጃ ለማሻሻል በክረምቱ ወቅት ተጀምሮ በነበረው "ትምህርት ለትውልድ " በሚል ንቅናቄ የትምህርት ጥራትን ማረጋገጥ የሚያስችል ለውጥ መመዝገቡን ገልፀዋል።    

በንቅናቄውም ክልሎች ሰፊ ሥራ መሥራታቸውን ያነሱት የቡድን መሪው፤ 14 ነጥብ 5 ቢሊየን ብር የሚሆን ኃብት መሰብሰቡን ጠቁመዋል። 

በዚህም በተለያዩ ክልሎች የቅድመ መደበኛ ትምህርት ቤቶች፣ የአንደኛ እና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች መገንባታቸውን ጠቁመዋል። 

ዩኒቨርሲቲዎችን በተልዕኮና የትኩረት አቅጣጫ መሠረት የመለየት ሥራ መከናወኑን ጠቁመው፤ የአፕላይድ፣ የምርምርና የአጠቃላይ ዩኒቨርሲቲዎች መሆናቸውንም ገልፀዋል። 

ዩኒቨርሲቲዎችም ከትኩረት መስካቸው አንጻር የትምህርት ፕሮግራሞችን በመቅረጽ ወደ ተግባር መግባት መጀመራቸውን ተናግረዋል። 

ለዚህም የደብረብርሃን ዩኒቨርሲቲና የኮተቤ ትምህርት ዩኒቨርሲቲዎች ተጠቃሽ ናቸው ብለዋል፡፡

ጉባዔው ነገ ኅዳር 19 ቀን 2016 ዓ.ም በተለያዩ ጉዳዮች ላይ በመምከር ይጠናቀቃል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም