ብሔራዊ አርበኝነትን መፍጠር የሚያስችል አሰባሳቢ ትርክት መገንባት ያስፈልጋል- አቶ ኦርዲን በድሪ

አዲስ አበባ ፤ ህዳር 18/2016 (ኢዜአ)፡- ብሔራዊ አርበኝነትን መፍጠር የሚያስችል አሰባሳቢ ትርክት መገንባት እንደሚያሰፈልግ የሀረሪ ክልል ርዕሰ መስተዳድር  ኦርዲን በድሪ ገለጹ።

 ርዕሰ መስተዳድሩ በአርባ ምንጭ የስልጠና ማዕከል እየተሰጠ በሚገኝው የአቅም ግንባታ ስልጠና መድረክ ላይ ተገኝተው ከመንግስት አመራሮች ጋር ውይይት አካሂደዋል።

በውይይት መድረኩ ላይ ርዕሰ መስተዳድሩ እንዳሉት የተዛቡ ትርክቶችን በማስተካከል ብሔራዊ አርበኝነትን መፍጠር የሚያስችል አሰባሳቢና የጋራ ትርክት መገንባት እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።

ሀገራዊ ብልጽግናን እውን ማድረግ የሚያስችል የሃሳብና የተግባር አንድነት መፍጠርም የስልጠናው ዓላማ መሆኑን አስረድተዋል።


 

አገራዊ ኢኮኖሚያዊ፣ የሰላምና ደህንነት፣ የሲቪል ሰርቪስ ማሻሻያ፣ የጊዜና ቴክኖሎጂ አጠቃቀም እንዲሁም ትኩረት የሚሹ አገራዊ፣ ቀጣናዊ፣ አህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ጉዳዮች ላይ አመራሩ በቂ ግንዛቤ በመያዝ የጋራ አቋም እንዲፈጠር የሚያደርጉ መሆናቸውን ተናግረዋል።

ይህም ለዘመናት ሲንከባለሉ የመጡ የኢትዮጵያ እዳዎችን በመቅረፍ ወደ ምንዳና ሃብት ለመቀየር ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው አንስተዋል።

ህዳር 14 የተጀመረው ስልጠናም እስከ ህዳር 26 ድረስ እንደሚቆይ የተገለፀ ሲሆን በስልጠናው ላይም ከሁሉም ክልሎች እና ከተማ አስተዳደር  የስራ ሀላፊዎች እየተሳተፉ መሆናቸውን ከሀረሪ ክልል መንግስት ኮሚኒኬሽን የተገኘው መረጃ ያመለክታል ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም