ዘላቂ ሰላም ለማረጋገጥ የሁሉም አካላት ተሳትፎ ወሳኝ ነው

አዲስ አበባ ፤ ህዳር 18/2016 (ኢዜአ)፦በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም ለማምጣት የሁሉም አካላት የጋራ ርብርብ እንደሚያስፈልግ የሰላም ሚኒስትሩ ብናልፍ አንዷለም ገለጹ።

በሰላም ሚኒስቴር የተዘጋጀው የሰላም ምክር ቤት ሁለተኛ ጉባዔ በአዲስ አበባ ተካሂዷል። 


 

በመድረኩ የሰላም ሚኒስትሩ ብናልፍ አንዷለምን ጨምሮ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነት እና ሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ዶክተር ዲማ ነገዎ፣ የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባዔና ሌሎች ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች ተወካዮች ተሳትፈዋል።

የሰላም ሚኒስትሩ ብናልፍ አንዷለም በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ የሰላም ሥራ የሁሉንም አካላት ርብርብ እና ጥረት የሚጠይቅ ሥራ ነው።

የሰላም ምክር ቤቱም ሁሉንም የኅብረተሰብ ክፍሎች በማካተት ሁሉም የራሱን አስተዋጽዖ እንዲያበረክት የሚያስችል መሆኑን ጠቁመዋል።

በኢትዮጵያ የተለያዩ ግጭቶች መከሰታቸውን አስታውሰው ከእነዚህ የግጭት አዙሪቶች እና ከደረሱ ጉዳቶች ትምህርት በመውሰድ ለሰላም አማራጭ ቅድሚያ መስጠት እንደሚያስፈልግ አመልክተዋል።

ማንኛውም ጥያቄ ያለው አካል በሰላማዊ መንገድ ቁጭ ብሎ በመነጋገር ለብዙ ችግሮች መፍትሔ ማምጣት ይቻላል ያሉት ሚኒስትሩ፤ ይህም  የመንግሥት ጽኑ አቋም መሆኑን ተናግረዋል።

መገናኛ ብዙኃን ለሰላም ግንባታ ሥራ ቁልፍ መሳሪያ መሆናቸውን ጠቅሰው፤ በኢትዮጵያም የተረጋጋ ሰላም እንዲመጣ አዎንታዊ ሚናቸውን ሊወጡ እንደሚገባ አመላክተዋል።

የውይይቱ ተሳታፊዎችም የተጀመሩ የሰላም ግንባታ ሥራዎችን አጠናክሮ መቀጠል ይገባል ብለዋል።

ሰላም እንዳይሰፍንና ቅሬታዎች እንዲባባሱ እየሰሩ ያሉ አካላት ተጠያቂ መሆን እንዳለባቸው ገልፀዋል።

የአንድ ቀን ጥፋት በርካታ ጉዳት የሚያመጣ በመሆኑ እለት ተለት በሰዎች ስነ-ልቦና ላይ መሠራት እንዳለበት ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም