የኮንትሮባንድ ንግድን በመከላከል ሂደት እንቅፋት የሚሆኑ  አመራሮችን በማጋለጥ ተጠያቂነትን ማረጋገጥ ይገባል 

101

አዲስ አበባ ፤ ህዳር 18/2016 (ኢዜአ) ፦ሀገርን ለችግር እየዳረገ በሚገኘው የኮንትሮባንድ እቃዎች ዝውውር የሚሳተፉ የመንግሥት አመራሮችን የማጋለጥና  ተጠያቂነትን ለማረጋገጥ  የሚደረገውን ጥረት ማገዝ እንደሚገባ የኢትዮጵያ ጉምሩክ ኮሚሽን  ኮሚሽነር ደበሌ ቃበታ ገለጹ።

በመጀመሪያው ሩብ ዓመት ከ3 ነጥብ 8 ቢሊዮን ብር በላይ የሚገመቱ የወጪና ገቢ የኮንትሮባንድ ዕቃዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውንም ተናግረዋል።

የመንግሥት የ2016 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ሩብ ዓመት የዕቅድ አፈጻጸም ሚኒስትር ዴኤታዎችና የተቋማት ኃላፊዎች በተገኙበት ተገምግሟል።

በግምገማው የኮንትሮባንድ እንቅስቃሴና ህገ-ወጥ ንግድ አሁንም ሀገሪቱን ለከፍተኛ ችግር እየዳረገ መሆኑ ተነስቷል።


 

 የቁም እንስሳት፣ የማዕድናት፣ የጫትና መሰል ምርቶች የኮንትሮባንድ ንግድን በበቂ ሁኔታ መቆጣጠር ያልተቻለበት ምክንያት ምንድን ነው ሲሉም ተሳታፊዎቹ ጠይቀዋል።

በዘላቂነት ችግሩን ለመፍታትም ስር ነቀልና የተቀናጀ ጥረት የሚጠይቅ መሆኑንም በስፋት አንስተዋል።

የኢትዮጵያ ጉምሩክ ኮሚሽን  ኮሚሽነር ደበሌ ቃበታ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ባለፉት ወራት ኮንትሮባንድና ህገወጥ ንግድን ለመከላከል ሰፋፊ ስራዎች ተከናውነዋል።

በዚህም 3 ነጥብ 8 ቢሊዮን ብር የሚገመቱ የወጪና ገቢ የኮንትሮባንድ እቃዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ገልጸዋል።

የኮንትሮባንድ የመከላከልና የቁጥጥር ስራዎች በተከታታይ እየተሰሩ ቢሆንም ችግሩ አሁንም  በዜጎች ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ  ላይ ተፅዕኖ መደቀኑን ጠቅሰዋል።

ባለፉት የለውጥ ዓመታት ኮንትሮባንድን መከላከልና መቆጣጠር የሚያስችሉ ጠንካራ የቁጥጥር ስርዓቶች ቢዘረጉም ችግሩ አሁንም  በተፈለገው መጠን አለመቀነሱን  ኮሚሽነሩ ተናግረዋል።

  በኮንትሮባንድ ንግድ ላይ የሚንቀሳቀሱ ግለሰቦች በቁጥጥር ስር እንዳይውሉ መረጃ አሳልፈው የሚሰጡ፣ በቁጥጥር ስር የዋሉትም እንዲለቀቁ የሚያደርጉና  በህግ እንዳይጠየቁ የሚሰሩ አመራሮች እንዳሉም ገልጸዋል።

በአንዳንድ አካባቢዎች ከዚህም የከፋ ተግባር ይፈጸማል ያሉት ኮሚሽነሩ ለአብነትም ለኮንትርባንድ ዝውውር እጀባ የሚሰጡ አካላት ስለመኖራቸው ጠቁመዋል።

በየአካበቢው ያሉ ኬላዎች የምርት ዝውውርን እያስተጓጎሉና ኮንትሮባንድን እያባባሱ በመሆናቸው እንዲነሱ  የተሰጠው አቅጣጫ  አለመተግበሩን ጠቅሰዋል።

በየኬላው ችግር የሚፈጥሩ አመራሮችንና ባለሙያዎችን በማጥራት እርምጃ እየተወሰደ ቢሆንም  ኮንትሮባንድን መከላከልና መቆጣጠር የሁሉንም ጥረት በመጠየቁ   በተፈለገው ደረጃ  ውጤት ያለመገኘቱን ገልጸዋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም