በካፋ ዞን ከ3 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በበጋ መስኖ ስንዴ ለማልማት ወደ ተግባር ተገብቷል 

ቦንጋ፤ ህዳር 18/2016 (ኢዜአ)፦ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል ካፋ ዞን ከ3 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በበጋ መስኖ ስንዴ ለማልማት ስራ መጀመሩ ተገለጸ።

ዞናዊ የዘንድሮ የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት ማስጀመሪያ መርሃ ግብር በጊምቦ ወረዳ  ተደራጅተው በበጋው ስንዴን ለማልማት በተዘጋጁ ወጣቶች ማሳ  ጉብኝት  ተካሂዷል።

የካፋ ዞን እርሻ፣ ደን፣ አካባቢና ህብረት ስራ ልማት መምሪያ ኃላፊ አቶ ጋዎ አባመጫ በዚህ ጊዜ እንደገለጹት በዞኑ ነዋሪውን ተጠቃሚ ለማድረግ ጥረቶች እየተደረጉ ነው።

በዘንድሮው የበጋ ወራት በ3 ሺህ 27 ሄክታር መሬት ላይ ስንዴ ለማልማት ወደ ስራ መገባቱን ገልጸው ከዚህም ከ121 ሺህ ኩንታል በላይ ምርት ለመሰብሰብ ግብ መያዙንም አክለዋል።

ስራው የተፈለገውን ውጤት እንዲያመጣ ግብዓትና ምርጥ ዘር በወቅቱ ከማቅረብ ጀምሮ አስፈላጊው ድጋፍና ክትትል እንደሚደርግ ገልጸዋል።

በመስጀመሪያ መርሃ ግብሩ ላይ የተገኙት የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አቶ እንዳሻዉ ከበደ በበኩላቸው በዘንድሮው የበጋ መስኖ ልማት ባለፉት ዓመታት ከተሰሩ ስራዎች ልምድ በመውሰድ የተሻለ ምርት ለመሰብሰብ መታቀዱን አንስተዋል።

"የምግብ ዋስትናችንን በአጭር ጊዜ ለማረጋገጥ ያሉንን የግብርና አማራጮች በሙሉ በመጠቀም ማልማት ላይ አተኩረናል'' ያሉት ዋና አስተዳዳሪው ከዚህ ውስጥ አንዱ የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት መሆኑንም ገልጸዋል።

በጊምቦ ወረዳ ከ750 ሄክታር በላይ መሬት ስንዴ ለማልማት ታቅዶ ወደስራ መገባቱን የተናገሩት ደግሞ የወረዳው ምክትል አስተዳዳሪ አቶ በላይ ባዩ ናቸው።

ከዚህም ከ26 ሺህ ኩንታል በላይ ምርት ለማግኘት ግብ መጣሉን ገልፀዋል።

ካለፉት ጊዜያት ልምድ በመቀመር የተሻለ ምርት ለማግኘት በሙሉ ፓኬጅ ለማልማት መታቀዱን ገልጸው ለዚህ የሚሆን ግብአት የማሰራጨትና የክትትል ስራ እየተሰራ ይገኛል ብለዋል ።

በጊምቦ ወረዳ ሀማኒ ቀበሌ በማህበር ተደራጅተው የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት የጀመሩ ማህበር አባል የሆነው ሻምበል ወንድማገኝ ሀይለሚካኤል፣ በ12 ሄክታር መሬት ላይ ስንዴን ለማልማት መጀመራቸውን ተናግረዋል።

በዞኑ ከዚህ ቀደም በዞኑ የበጋ መስኖ ልማት እምብዛም ያልተለመደ እና በዚህ ዓመት ከጥምር ግብርና ጋር በቅንጅት የሚሰራ መሆኑም ተመልክቷል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም