በቴክኒክና ሙያ ሥልጠና የሙያ ማማከርና የድጋፍ አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችል መመሪያ ይፋ ሆነ  

አዲስ አበባ ፤ ህዳር 18/2016 (ኢዜአ)፡-የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር በቴክኒክና ሙያ ሥልጠና የሙያ ማማከርና የድጋፍ አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችል መመሪያ ይፋ አደረገ። 

የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር መመሪያው የጀርመን የልማት ተራድኦ ድርጅት (ጂ አይ ዜድ) እና ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር ያዘጋጀው ነው ተብሏል። 


 

መመሪያው በዘርፉ የመማር ማስተማር ሂደቱን የሚያሻሽልና ተማሪዎች ያላቸውን ክህሎት አውጥተው እንዲጠቀሙ ትልቅ አቅም የሚፈጥር መሆኑንም ነው የተመላከተው።  

የሥራና ክህሎት ሚኒስትር አማካሪ ተሾመ ለማ በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት፤ መመሪያው ተማሪዎች ሙያዊ ክህሎታቸውን ተጠቅመው ውጤታማ ሥራ ፈጣሪ እንዲሆኑ ያግዛቸዋል ብለዋል።

ወጣቶች በዕውቀት፣ በልምድ፣ በራስ አገዝ የሥራ ክህሎት ብቁ እንዲሆኑ፣ የሥራ ፈጠራ ስትራቴጂዎችን እንዲያጤኑና ውሳኔ ሰጪነት ላይ ያላቸውን ልምድ እንዲያዳብሩም ያስችላል ነው ያሉት። 

በጀርመን የልማት ተራድኦ ድርጅት (ጂ አይ ዜድ) የኢትዮ-ጀርመን የትምህርትና ሥልጠና መርሃ-ግብር አስተባባሪ አሊ ሙሃመድ ካሃን በበኩላቸው፤ መመሪያው በቴክኒክና ሙያ ሥልጠና የሚያልፉ ወጣቶችንና ሥራ ፈጣሪዎችን ይበልጥ ውጤታማ ያደርጋቸዋል ሲሉ ገልፀዋል። 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም