በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ሙስናና ብልሹ አሠራርን ለመከላከል ህብረተሰቡን ያሳተፈ ትግል ይደረጋል 

አርባ ምንጭ፤ህዳር 18/2016 (ኢዜአ):-በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የሙስናና ብልሹ አሠራርን ለመከላከል የህብረተሰብን ተሳትፎ ማጠናከር ላይ ትኩረት አድርጎ እየሰራ መሆኑን የክልሉ ስነ-ምግባርና ፀረ-ሙስና ኮሚሽን ገለጸ ።

“ሙስና የጋራ ጠላታችን ነው በህብረት እንታገል” በሚል መሪ ሀሳብ 20ኛው ዓለም አቀፍ የፀረ- ሙስና ቀን በአርባምንጭ ተከብሯል።

የክልሉ ስነ-ምግባርና ጸረ-ሙስና ኮሚሽን ኮሚሽነር ሶፎኒያስ ደስታ በዚህ ጊዜ እንዳሉት ሙስናና ብልሹ አሰራር የመከላከል ስራው ከግብ እንዲደርስ የህብረተሰብ ተሳትፎ ወሳኝ ሚና አለው።

በመሆኑም ትግሉ የተፈለገውን ውጤት እንዲያመጣ ኮሚሽኑ የህዝብ ተሳትፎን ማጠናከር ላይ አትኩሮ እየተሰራ እንደሚገኝ ነው የገለጹት።

''ሙስናና ብልሹ አሠራር የክልሉን ዕድገትና ልማት በመግታት በዜጎች ተጠቃሚነት ላይ አሉታዊ ጫና የሚያሳድር የጋራ ጠላታችን ነው'' ያሉት ኮሚሽነሩ "ሙስናን በመከላከል ረገድ ባለቤት የሆነውን ማህበረሰብ በማሳተፍ ጠንካራ ትግል ለማድረግ እየተሠራ ይገኛል" ብለዋል።

በትምህርት ቤቶች፣  በሃይማት ተቋማት፣ ሲቪክ ማህበራት በኩል ሰፊ የግንዛቤ ሥራ እየተከናወነ መሆኑንም አስታውቀዋል፡፡

ይህን ለማጠናከር የተጀመረው ተግባር ውጤት እያመጣ መሆኑን ጠቁመው ባለፉት 3 ወራት ሀሰተኛ የትምህርት ማስረጃ፣ በመሬት አስተዳደር፣ በግዥና ሌሎች ዘርፎች ከ10 በላይ ጥቆማዎች ቀርበው የማጣራት ስራ እየተካሄደ እንደሚገኝ ጠቁመዋል።

ሙስናና ብልሹ አሠራርን ለማስወገድ ህዝብና መንግስት ተቀናጅተው መስራት እንዳለባቸው የገለጹት ደግሞ በኮሚሽኑ የትምህርትና ስልጠና ባለሙያ አቶ ፋሲል ጌታቸው ናቸው፡፡

በመንግስት ተቋማት የግዥ፣ የአገልግሎት አሰጣጥ፣ የገቢ ግብር፣ የትምህርት ማስረጃ አሰጣጥ፣ የመሬት አስተዳደር ስርአት፣ የኢንቨስትመንት ፈቃድና ሌሎች ለሙስና ተጋላጭ በሆኑ ዘርፎችና  ተቋማት ሙስና እንዳይፈጸም ክትትል እየተደረገ መሆኑንም ገልጸዋል። 

ሙስናን መዋጋት የህልውና ጉዳይ በመሆኑ በመከላከሉና ህጋዊ እርምጃ እንዲወሰድ ከማድረግ አንጻር ተቋማቱ ከህብረተሰቡ ጋር ተቀናጅተው መሥራት እንደሚገባቸው ጠቁመዋል፡፡

በአርባ ምንጭ ከተማ የኦሞ ባንክ ሠራተኛ የሆኑት አቶ ታከለ ምትኩ፣ መገናኛ ብዙሃን በሙስና አስከፊነትና መከላከሉ ላይ ለህብረተሰቡ ግንዛቤ በመስጠት እንዲሁም ችግሮችን መርምሮ በማጋለጥ የበኩላቸውን ሊወጡ እንደሚገባ አሳስበዋል።

በተቋማቸውም ሆነ በአከባቢያቸው ከብልሹ አሠራርና ሙስና ጋር በተያያዘ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለሚመለከተው ክፍል በመጠቆም የበኩላቸወን እንደሚወጡም ጠቁመዋል፡፡ 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም