በአማራ ክልል ከቱሪዝም ዘርፍ የሚገኘውን ገቢ ማሳደግ የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑ ተገለጸ

115

ደሴ ፤ ህዳር 18/2016(ኢዜአ):- በአማራ ክልል የቱሪስት መዳረሻ ቦታዎችን በማስተዋወቅና የቱሪስቶችን የቆይታ ጊዜ በማራዘም ከዘርፉ የሚገኘውን ገቢ ለማሳደግ የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን የክልሉ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ አስታወቀ፡፡

"ቱሪዝም ለአረንጓዴ ልማት፣ አረንጓዴ ልማት ለቱሪዝም" በሚል መሪ ሃሳብ የቱሪዝም ዘርፍ እድገት ላይ ያተኮረ ውይይት በደሴ ከተማ ተካሄዷል።

የቢሮው ኃላፊ አቶ ጣሂር መሃመድ እንደገለጹት፤ በክልሉ የቱሪዝም መዳረሻ ቦታዎችን በማልማት፣ ቅርሶችን በመጠበቅ ለጎብኝዎች ምቹ ለማድረግ እየተሰራ ነው፡፡

በክልሉ ለቱሪዝም መዳረሻ የሚሆኑ በርካታ ታሪካዊ፣ ሀይማኖታዊና ተፈጥሯዊ ፀጋዎች ቢኖሩም፤ ዘርፉ በሚፈለገው ልክ ባለመተዋወቁና ባለመልማቱ ገቢው ማደግ አለመቻሉን ገልፀዋል።

በመሆኑም ቀጣይ ሰፊ ንቅናቄ በመፍጠርና መዳረሻ ቦታዎችን በተገቢው መንገድ በማስተዋወቅ ቱሪዝምን የማነቃቃት ስራ ይከናወናል ብለዋል።

በተለይም ሾንኬ፣ ተድባበ ማሪያም፣ ሀርቡ ፍል ውሃ፣ ጀማ ንጉስና ሌሎች አዳዲስ የቱሪስት መዳረሻ ቦታዎችን በማስተዋወቅ የጎብኝዎችን ቁጥር ማሳደግና የቆይታ ጊዜያቸውን ማራዘም የሚያስችሉ ተግባራት ይከናወናሉ ነው ያሉት።


 

እንደ ቢሮ ኃላፊው ገለጻ፤ ከፈረንሳይ መንግስት ጋር በተያዘው ውልና ስምምነት መሰረት የላልይበላ ቅርስ እድሳት እየተከናወነ ነው።

የደቡብ ጎንደር ዞን ባህልና ቱሪዝም መምሪያ ኃላፊ ተወካይ አቶ ሲሳይ ገደፋው በበኩላቸው፤ በዞኑ ለቱሪስት መዳረሻ ምቹ የሆኑ የቱሪዝም ሃብቶችን በማስተዋወቅ ለጎብኝዎች ምቹ የማድረግ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በአካባቢው ጉና ተራራንና የቅኔ ትምህርት ቤቶችን ጨምሮ በርካታ ሳቢና ማራኪ መዳረሻ አካባቢዎችን በማልማትና በማስተዋወቅ በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

''በአካባቢያችን የሚገኙ የቱሪስት መዳረሻ ቦታዎችን በማልማት፣ ቅርሶችን በመጠበቅና በማስተዋወቅ ገቢ ማመንጨት እንዲችሉ እየተሰራ ነው'' ያሉት ደግሞ የደብረ ብርሃን ከተማ አስተዳደር ባህልና ቱሪዝም መምሪያ ኃላፊ ተወካይ አቶ አክሊል ጌታቸው ናቸው፡፡

በመርሃ ግብሩ ላይ የክልልና የዞን አመራር አባላትና ባለሙያዎችን ጨምሮ የሃይማኖት አባቶች፣ የአገር ሽማግሌዎችና ባለድርሻ አካላት እየተሳተፉ ሲሆን፤ በነገው ዕለት የተለያዩ የቱሪስት መዳረሻ ቦታዎች ይጎበኛሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም