በደብረ ብርሀን ከተማ  በበጋ በጎ ፈቃድ አገልግሎት 27 ሺህ 800 ወጣቶች ይሳተፋሉ

ደብረ ብርሀን  ህዳር 18/2016 (ኢዜአ)፡- በደብረ ብርሃን ከተማ 27 ሺህ 800 ወጣቶች የሚሳተፉበት የበጋ በጎ ፈቃድ አገልግሎት መርሃ ግብር ማስጀመሪያ ተካሄደ።

የደብረ ብርሃን ከተማ አስተዳደር ወጣቶችና ስፖርት መምሪያ ሀላፊ አቶ አውራሪስ አረጋ ዛሬ በተካሄደው የውይይት መድረክ ላይ እንደገለጹት፤ በክረምት ወቅት የተካሄደውን የበጎ ፈቃድ አገልግሎት በበጋ ወራት አጠናክሮ ለማስቀጠል ወደ ተግባር ተገብቷል።

በዚህም በበጋ ወራት 27 ሺህ 800  በጎ ፈቃደኛ ወጣቶች ህብረተሰቡን ተጠቃሚ በሚያደርጉ የማህበራዊ አገልግሎትና የልማት ስራዎች ላይ እንደሚሳተፉ አቶ አውራሪስ ተናግረዋል።

በወጣቶቹ ከሚከናወኑ ተግባራት መካከል 77 በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ለሚገኙ ነዋሪዎችና አረጋውያን አዲስ የመኖሪያ ቤት ግንባታና  የ117 ያረጁ ቤቶች እድሳት እንደሚገኙበት ተናግረዋል።

ደም ልገሳ፣ የተተከሉ ችግኞችን መንከባከብ፣ የመንገድ ስራ ጨምሮ በጤና፣ በትምህርትና በሌሎች ዘርፎች  የልማት ስራዎች እንደሚተገበሩ አመልክተዋል።

በዚህ ተግባር “ከ98 ሺህ በላይ የህብረተሰብ ክፍሎች ተጠቃሚ ይሆናሉ” ተብሎ እንደሚጠበቅ ኃላፊው አስታውቀዋል።

የከተማ አስተዳደሩ ምክትል ከንቲባ አቶ ወርቃለማሁ ኮስተሬ በበኩላቸው፤ የበጎ ፈቃድ ተግባራት ወጣቶች ወገኖቻቸውን በቅን ልብ የሚያገለግሉበት መሆኑን ተናግረዋል።

"ወጣቶች የተጀመሩ የሰላም፣ የልማትና የዲሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ስራዎችን አጠናክረው በማስቀጠል የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ መስራት አለባቸው" ብለዋል።

ከተማ አስተዳደሩ በወጣቶች ለሚከናወኑ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ተግባራት ስኬታማነት ተገቢውን እገዛና ድጋፍ እንደሚያደርግ አስታውቀዋል።

“ከበጋ ወራት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት በተጨማሪ የልማት ስራዎችን በማከናወን የአካባቢውን ሰላም ለማጽናት እንሰራለን'' ያለው ደግሞ የከተማው ነዋሪ ወጣት ተስፉ ውብሸት ነው።

ወጣት ቤቴልሄም ሸዋየ በበኩሏ፤"በከተማ አስተዳደሩ የሚገኙ ታሪካዊና ሀይማኖታዊ ስፍራዎችና ቅርሶችን በመንከባከብ ለቱሪዝም ዘርፍ አመቺ እንዲሆኑ እንሰራለን" ብላለች።

በከተማ አስተዳደሩ በክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት 50 ነጥብ 1 ሚሊዮን ብር ግምት ያላቸው የማህበራዊና የልማት ስራዎች መከናወናቸው በውይይቱ ተመላክቷል ።

በውይይት መድረኩ የከተማ አስተዳደሩ አመራር አባላትና ወጣቶች የተገኙ ሲሆን፤ በክረምት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት የጎላ ሚና ላበረከቱ ወጣቶችና ድርጅቶች የእውቅና ምስክር ወረቀት ተበርክቶላቸዋል።  

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም