ቀጥታ፡

በበጎ ፈቃደኞች አማካኝነት የመኖሪያ ቤት ችግራችን በመፈታቱ የተሻለ ህይወት መምራት ጀምረናል - አረጋውያን

ሀዋሳ፤ ህዳር 18/2016 (ኢዜአ)፦ በበጎ ፈቃደኞች አማካኝነት የረጅም ጊዜ የመኖሪያ ቤት ችግራችን በመፈታቱ የተሻለ ህይወት መኖር ጀምረናል ሲሉ በሲዳማ ክልል በበጎ ፈቃድ አገልግሎት ቤታቸው የታደሰላቸው አረጋዊያንና በዝቅተኛ ኑሮ ውስጥ የሚገኙ ነዋሪዎች ገለጹ፡፡

በክልሉ የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት መርሃ ግብር ከ1 ሺህ 200 በላይ የመኖሪያ ቤቶች ዕድሳትና ግንባታ የተከናወነ ሲሆን፤ ለአረጋውያንና በዝቅተኛ ኑሮ ደረጃ ላይ ለሚገኙ ነዋሪዎች መሰጠቱን የሴቶች፣ ወጣቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ አስታውቋል፡፡


 

የሲዳማ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ደስታ ሌዳሞ ከሌሎች የክልሉ ከፍተኛ አመራር አባላት ጋር በመሆን በበጎ ፈቃድ አገልግሎቱ ቤታቸው የታደሰላቸውን አረጋዊያንና በዝቅተኛ ኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ ነዋሪዎችን ጎብኝተዋል፡፡

በክረምት ወራት በበጎ ፈቃድ አገልግሎት ቤታቸው ከታደሰላቸው ነዋሪዎች መካከል ወይዘሮ ብዙነሽ መልሳሞ እንደገለጹት፤ ከልጆቻቸውና ከህመምተኛ ባለቤታቸው ጋር በደሳሳ ጎጆ ይኖሩ ነበር፡፡

"ለተደረገልን በጎነት እኛ መክፈል አንችልም" ያሉት የለኩ ከተማ ነዋሪዋ ወይዘሮ ብዙነሽ፤ በጎ አድራጊዎችና ጠያቂ ሰዎች እንዳሉ "እንዲሰማኝ ስላደረጉ አመሰግናለሁ" ብለዋል፡፡

ሌላኛው የይርጋለም ከተማ ነዋሪ የእድሜ ባለጸጋ ወይዘሮ ደብሪቱ አለሙ በበኩላቸው እንደገለጹት፤ ለዓመታት በፈረሰ ቤታቸው ሲኖሩ ቆይተዋል። የረዥም ጊዜ ጥያቄያቸው በህይወት እያሉ ምላሽ በማግኘቱ ደስተኛ ሆነዋል።

አቅማቸው እንደዛሬው ባልደከመ ጊዜ ኑሯቸውን ለመግፋት የተገኘውን ስራ ሰርተው ያሳለፉ ሲሆን፤ እርጅና ሲጫጫናቸው የሚደግፋቸው በማጣት ሲቸገሩ መቆየታቸውን ገልጸዋል፡፡

የፈረሰው ቤታቸው በበጎ ፈቃደኞች እንደ አዲስ መገንባቱን ጠቅሰው፤ ይህም ቀሪ እድሜያቸውን በደስታና ተስፋ እንዲኖሩ በማድረጉ ሁሉንም አመስግነዋል፡፡


 

በዳሌ ወረዳ የሶያማ ቀበሌ ነዋሪ ወጣት አዲሱ ብሩ በክረምት የወጣቶች በጎ ፈቃድ አገልግሎት ከጓደኞቹ ጋር በመቀናጀት በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ የሚኖሩትንና የአረጋዊያንን ቤት የማደስ ተግባር ማከናወኑን ጠቅሷል፡፡

"በጎነት ለራስ ነው" ያለው ወጣት አዲሱ፤ አረጋውያንን ማገዝና መርዳት "የኢትዮጵያውያን ነባር ባህል ከመሆን ባለፈ ለአዕምሮ እርካታን የሚሰጥ ተግባር ነው" ብሏል፡፡

የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ደስታ ሌዳሞ በበኩላቸው፤ ክልሉ አቅም ለሌላቸው ወገኖች የሚያደርገውን ድጋፍ ህዝቡን በማስተባበር አጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል፡፡


 

በክልሉ በተከናወነው የበጎ ተግባር ስራ ወጣቶች ከፍተኛ አስተዋጽኦ በማበርከታቸው ምስጋና ያቀረቡት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ ዞኖችና ወረዳዎችም ስራውን በማስተባበርና በማገዝ ትልቅ ድርሻ ማበርከታቸውን ገልጸዋል፡፡

በበጎ ተግባር ስራው በየአካባቢው ያለው አፈጻጸም የተለያየ ቢሆንም "የተገኙ ተመክሮዎችን ማስፋት ይገባል" ብለዋል፡፡

በክልሉ የተጀመረውን የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ስራ ቀጣይነት እንዲኖረው መላ ህዝቡን የማሳተፍ ስራ ትኩረት እንደሚደረግበት ጠቁመው፤ በዚህም የሚያጋጥሙ ችግሮችን በጋራ መፍታት እንደሚቻል ተናግረዋል፡፡  


 

የክልሉ ሴቶች፣ ወጣቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ሃላፊ ወይዘሮ እመቤት ኢሳያስ በበኩላቸው፤ በ2015 የክረምት ወራት በጎ ፈቃድ አገልግሎት በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ ነዋሪዎችና አረጋዊያን መኖሪያ ቤት ግንባታን ጨምሮ በተለያዩ 13 ዘርፎች ሲሰራ መቆየቱን ተናግረዋል፡፡

የበጎ ፈቃድ አገልግሎት በክልሉ የበርካታ ነዋሪዎችን ችግር በማቃለል እፎይታ እየሆነ መምጣቱን አንስተው፤ ተግባሩ ከሚሰጠው መንፈሳዊና ማህበራዊ መስተጋብር አኳያ ልምድ እየሆነ መምጣቱን አክለዋል ፡፡

በክልሉ የክረምት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ከ761 ሺህ በላይ ወጣቶች  መሳተፋቸውን ተናግረዋል፡፡

በቤት እድሳትና ግንባታ በተከናወነው ተግባር ብቻ ከ5 ሺህ በላይ የህብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን ጠቅሰው፤ በተጨማሪም ከ2 ሺህ 216 ዩኒት በላይ ደም መሰብሰቡን ተናግረዋል፡፡

በክረምት ወራት በተከናወኑ የበጎ ፈቃድ አገልግሎቶች ከ749 ሚሊዮን ብር  በላይ የህዝብና የመንግስት ሃብት ማዳን መቻሉንም ገልፀዋል። 

በአለታ ወንዶ በተካሄደው የማጠቃለያ መድረክ በክረምት ወጣቶች በጎ ፈቃድ አገልግሎት ድርሻ ያበረከቱ ተቋማት እውቅና የተሰጠ ሲሆን፤ በተሰሩ ስራዎች ላይም ውይይት ተደርጓል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም