ቀጥታ፡

ባህርዳር ዩኒቨርሲቲ ለአራት ዶክተሮች  የሙሉ ፕሮፌሰርነት ማዕረግ ሰጠ

ባህርዳር ፤ህዳር 18 /2016 (ኢዜአ)፡-  ባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ  በተሰማሩባቸው ዘርፎች የላቀ አስተዋጽኦ ላበረከቱ አራት ዶክተሮች  የሙሉ ፕሮፌሰርነት የማዕረግ ዕድገት መስጠቱን አስታወቀ።

የዩኒቨሲቲው አስተዳደር ቦርድ የሙሉ ፕሮፌሰርነት ማዕረግ ዕድገትን የሰጠው ለዶክተር እሰይ ከበደ፣ ለዶክተር ደለለ ወርቁ፣ ለዶክተር ሰሎሞን ወርቅነህና ለዶክተር አወቀ ስዩም ነው። 

ምሁራኑ በመማርና ማስተማር፣ ችግር ፈቺ ምርምርና በማህበረሰብ አገልግሎት ውጤታማ ስራ ማከናወናቸውን የዩኒቨርሲቲው የኢንፈርሜሽንና ኮሙዩኒኬሽን ስትራቴጂክ ምክትል ፕሬዚዳንት ዶክተር ዘውዱ ዕምሩ ለኢዜአ ገልጸዋል። 

ለዚህም ዶክተር ዕሰይ ከበደና ዶክተር አወቀ ስዩም በ"ባዮስታትስቲክስ"፣ ዶክተር ደለለ ወርቁ በ"ኢንኦርጋኒክ ኬሚስትሪ" እና ዶክተር ሰሎሞን ወርቅነህ ደግሞ በ"ባዮሲስተም ኢንጂነሪንግ " ችግር ፈቺ ስራዎችን ማከናወናቸውን አስረድተዋል።

ምሁራኑ በርከት ያሉ የምርምር ስራዎቻቸውም ዓለም አቀፍ ዕውቅና ባላቸው የህትመት ጆርናሎች ማሳተም መቻላቸውን አመልክተው፤ የአካባቢውን ማህበረሰብ ችግሮች የሚፈቱ ስራዎችን ማከናወናቸው  አብራርተዋል። 

ዩኒቨርሲቲው የአስተዳደር ቦርድ የምሁራኑን አፈጻጸም ገምግሞ  በተሰማሩባቸው ዘርፎች ለዩኒቨርሲቲውና ለሀገራቸው ላበረከቱት የላቀ አስተዋጽኦ  የሙሉ ፕሮፌሰርነት ማዕረግ  መሰጠቱን አስታውቀዋል።

ዩኒቨርሲቲው እንደ አውሮፓ አቆጣጠር በ2030 በአፍሪካ  ደረጃ ግንባር ቀደም የምርምር ተቋም  ለመሆን አቅዶ እየሰራ መሆኑን ጠቅሰው፤ ለዚህም የምሁራኑ ድርሻ የጎላ መሆኑን አመልክተዋል። 

ባህርዳር ዩኒቨርሲቲ  በተለያዩ የትምህርት መርሃ ግብሮች 40 ሺህ የሚሆኑ ተማሪዎችን እያስተማረ እንደሚገኝም ተጠቅሷል።

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም