በመዲናዋ የሚገኙ የጫኝና አውራጅ ማኅበራት የህብረተሰቡ የጸጥታ ስጋት እንዳይሆኑ ስርዓት ተበጅቷል

አዲስ አበባ ፤ ህዳር 18/2016 (ኢዜአ) ፦በአዲስ አበባ የሚገኙ የጫኝና አውራጅ ማኅበራት የህብረተሰቡ የፀጥታ ሥጋት ከመሆን ይልቅ የማኅበረሰቡ አጋልጋይና የሰላም ዘብ እንዲሆኑ ስርዓት መዘርጋቱን የአዲስ አበባ ሰላምና ፀጥታ አስተዳደር ቢሮ ኃላፊ ሊዲያ ግርማ ገለጹ።

የአዲስ አበባ ሰላምና ፀጥታ አስተዳደር ቢሮ የጫኝና አውራጅ ማህበራት የአገልግሎት አሰጣጥን ለመከታተልና ለመቆጣጠር በወጣው መመሪያ ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት አካሂዷል።


 

ከዚህም በተጨማሪ በመዲናዋ በተመረጡ አምስት ክፍለ ከተሞች በሚገኙ የጫኝና አውራጅ ማህበራት ላይ በተደረገው ክትትልና ድጋፍ የተስተዋሉ ክፍተቶች ለውይይት ቀርበዋል። 

የቢሮው ኃላፊ ሊዲያ ግርማ በዚሁ ወቅት እንደተናገሩት በመዲናዋ የተደራጁ ጫኝና አውራጅ ማኅበራት በወጣው መመሪያ መሠረት በተቀመጠላቸው የመጫንና የማውረድ ተግባር ላይ ብቻ ይሰማራሉ።

በመዲናዋ በጫኝና አውራጆች ይታይ የነበረውን  ያልተገባ አሰራር ተከትሎ ማህበረሰቡ ለፀጥታ መደፍረስና መጉላላት ተዳርጎ እንደቆየ አስታውሰዋል።

ይህንንም ችግር ለመቅረፍ በሁሉም ክፍለ ከተሞች የጫኝና አውራጅ ማኅበራትን መልሶ ለማደራጀት የተሰራው ስራ በተሳካና በተደራጀ መልኩ መከናወኑን አመልክተዋል።

መመሪያው ሕዝቡ ሲያነሳቸው የነበሩ ቅሬታዎች በመቅረፍ ሥርዓት ያለው አሰራር ለመፍጠር ያስችላል ብለዋል። 

በጫኝና አውራጅ የተደራጁ ማኅበራት የፀጥታ ሥጋት ከመሆን ይልቅ ለማኅበረሰቡ የሰላም ዘብና አገልጋይ እንዲሆኑ የጋራ ትብብር እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።

ማኅበራቱ የመዲናዋ ነዋሪ የፀጥታ ጠባቂና ተባባሪ አካል የሚሆኑበት ሥርዓት እንደሚዘረጋም የቢሮ ኃላፊዋ ሊዲያ ግርማ አመላክተዋል።

በሕግና በሥርዓት ተገዥ ሆነው የማይሰሩ ማኅበራት በሕግ ተጠያቂ እንደሚሆኑ የቢሮ ኃላፊዋ ሊዲያ ግርማ ተናግረዋል።


 

የቢሮው ምክትል ኃላፊ ሚደቅሳ ከበደ በበኩላቸው መመሪያው በከተማዋ የሚስተዋለውን ሥርዓት አልበኝነት ወደ ሥርዓት ለማምጣት ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር የሚረዳ  መሆኑን ተናግረዋል።

የመዲናዋ ነዋሪ ላልተገባ እንግልት መዳረግ የለበትም ያሉት አቶ ሚደቅሳ በመመሪያው መሠረት የጫኝና አውራጅ ማኅበራትን ሥርዓት ለማስያዝ በቅንጅት መሥራት እንደሚገባ አሳስበዋል።

ነዋሪው በመመሪያው መሠረት የወጣውን ተመን በመረዳት ኃላፊነቱን እንዲወጣ ለማስቻል የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራው ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም