ቀጥታ፡

ምክር ቤቱ የአዋሽ-ኮምቦልቻ-ሃራ-ወልዲያ የምድር ባቡር መስመር ዝርጋታ እንዲጠናቀቅ ማሳሰቢያ ሰጠ

አዲስ አበባ ፤ ህዳር 18/2016 (ኢዜአ) ፦ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት የልማት ድርጅቶች ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የአዋሽ-ኮምቦልቻ-ሃራ-ወልዲያ የምድር ባቡር መስመር ዝርጋታ በፍጥነት ተጠናቅቆ አገልግሎት እንዲሰጥ ማድረግ እንደሚገባ አሳሰበ።

ቋሚ ኮሚቴው የኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽንን የ2016 በጀት ዓመት ዕቅድና የአንደኛ ሩብ ዓመት ሥራ አፈፃፀም ሪፖርት እንዲሁም የቀጣይ ፍኖተ ካርታን ገምግሟል፡፡

በመደረኩም ቋሚ ኮሚቴው ኮርፖሬሽኑ ያሉበትን ዘርፈ ብዙ ችግሮች በመፍታት ተጨባጭ ውጤት ለመምጣት በትኩረት መስራት እንደሚገባው አሳስቧል።

ያለበትን የዕዳ ጫና በመቀነስ እና የውስጥ ገቢንና የፋይናንስ አቅምን በማጠናከር የተጀመሩ ፕሮጀክቶችን ለማጠናቀቅ በትኩረት መስራት እንዳለበት ተገልጿል።

የአዋሽ-ኮምቦልቻ-ሃራ-ወልዲያ የምድር ባቡር መስመር ዝርጋታ 93 በመቶ መድረሱን በሪፖርቱ የተመለከተው ቋሚ ኮሚቴው፤ ኮርፖሬሽኑ ቀሪውን ሰባት ፐርሰንት አጠናቅቆ መንገዱ አገልግሎት እንዲሰጥ ማድረግ እንዳለበት አሳስቧል::

ኮርፖሬሽኑ መሬት አያያዝና አጠቃቀም እንዲሁም ከጥገና አገልግሎት መሣሪያዎች ጋር በተያያዘ ያሉበትን ክፍተቶች ለማረም ከክልሎችና ከከተማ አስተዳዳሮች ጋር በቅንጅት መስራት እንዳለበትም የቋሚ ኮሚቴው አባላት ጠቁመዋል።

በኮርፖሬሽኑ ቢዝነስና ዲቨሎፕመንት ዘርፍ ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚ ኢንጂነር ጌቱ ግዛው እንደገለጹት ተቋሙ ዓለም አቀፋዊና አህጉራዊ ልምድና ተሞክሮን ባገናዘበ መልኩ ጠንካራ ሀገራዊ የምድር ባቡር ለመገንባት እየሰራ ነው።


 

በሰሜኑ የሀገራችን ክፍል ተከስቶ የነበረው ጦርነት ተፅዕኖ እንደነበረውና በንብረቶች ላይ ከፍተኛ የሆነ ስርቆትና ውድመት መድረሱን ጠቁመው አሁን ላይ ብዙ ንብረቶችን በማስመለስ አዋሽ-ከምቦልቻ-ሃራ-ወልዲያ ያለውን ፕሮጀክት ለማጠናቀቅ እንደሚሰራ መግለጻቸውን ከህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

በኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽን የባቡር ኔትወርክ ዘርፍ ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚ ኢንጂነር ሥላስ ካሣ በበኩላቸው፤ በውጭ ምንዛሪ ዕዳ እና በብድር ወለድ ጫና ምክንያት የቆሙ ፕሮጀክቶች ወደ ሥራ እንዲመለሱ ቋሚ ኮሚቴው የበኩሉን እገዛ እንዲያደርግ ጠይቀዋል፡፡

የኢትዮጵያ የምድር ባቡር 6 መቶ 56 ኪሎ ሜትር እንደሚሸፍንና በቀጣይ ወደ 1 ሺህ 2 መቶ 66 ኪሎ ሜትር ለማድረስ መታቀዱን የኮርፖሬሽኑ የሥራ ኃላፊዎች ገልፀዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም