ለፋይናንስ አቅርቦት ተደራሽነትና ለስራ እድል ፈጠራ አነስተኛ ብድርና ቁጠባ ተቋማት የላቀ ሚናቸውን ሊወጡ ይገባል

አዲስ አበባ ፤ህዳር 18/2016 (ኢዜአ) ፡-ለፋይናንስ አቅርቦት ተደራሽነትና ለዜጎች የስራ እድል ፈጠራ አነስተኛ ብድርና ቁጠባ ተቋማት ሚናቸውን አጠናክረው ሊቀጥሉ እንደሚገባ የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ዴኤታ ንጉሱ ጥላሁን ገለጹ።

የኢትዮጵያ አነስተኛ ብድርና ቁጠባ ተቋማት ማህበር 25ኛ ዓመት የምስረታ በዓሉን በተለያዩ ዝግጅቶች እያከበረ ይገኛል።

እለቱን በማስመልከት የዘርፉን እንቅስቃሴ የሚያሳይ አውደ ርእይ የተከፈተ ሲሆን የአነስተኛ የፋይናንስ ተቋማት ለኢኮኖሚና ማህበራዊ ልማት ያላቸውን አስተዋጽኦ በሚመለከት ውይይት ተካሂዷል።

የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር  ሚኒስትር ዴኤታ ንጉሱ ጥላሁን፤ በመድረኩ ላይ ባስተላለፉት መልእክት የአነስተኛ ብደርና ቁጠባ ተቋማት በሀገር ልማት ላይ የላቀ አስተዋጽኦ እንዳላቸው አንስተዋል።

በተለይም ለጥቃቅንና አነስተኛ እና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች የፋይናንስ አቅርቦት ተደራሽነትና ለዜጎች የስራ እድል ፈጠራ ተቋማቱ የላቀ ሚና አላቸው ነው ያሉት።

በመሆኑም ለፋይናንስ አቅርቦት ተደራሽነትና ለዜጎች የስራ እድል ፈጠራ አነስተኛ ብድርና ቁጠባ ተቋማት ሚናቸውን አጠናክረው ሊቀጥሉ ይገባል ብለዋል።

የኢትዮጵያ አነስተኛ ብድርና ቁጠባ ተቋማት ማህበር ዋና ስራ አስፈጻሚ ተሾመ ከበደ፤ የማህበሩ 25ኛ ዓመት የምስረታ በዓል ለቀጣይ ሶስት ቀናት በልዩ ልዩ ዝግጅቶች መከበሩ ይቀጥላል ብለዋል።

የተቋማቱን አገልግሎት ዘመናዊና ቀልጣፋ በማድረግ አሰራራቸውን ማዘመንና ተደራሽነታቸወን ማስፋት በቀጣይ ትኩረት ይደረጋል ሲሉም ገልጸዋል።

በተለይም ለሴቶች የፋይናንስ አቅርቦትና ተደራሽነትን በማመቻቸት ከራሳቸው ባለፈ ለሀገር ልማት የሚኖራቸውን አስተዋጽኦ ለማሳደግ እንሰራለን ሲሉ አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ አነስተኛ ብድርና ቁጠባ ተቋማት ማህበር 25ኛ ዓመት የምስረታ በዓል "ማይክሮ ፋይናንስ በዲጂታል ዘመን የፋይናንስ አካታችነት ለስራ ፈጠራና ለሴቶች የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት” በሚል መሪ ሃሳብ በተለያዩ ዝግጅቶች መከበሩ የሚቀጥል ይሆናል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም