በቴክኖሎጂ የታገዘና አዳዲስ የክፍያ ስርአት በመተግበሩ የግብር ክፍያውን ስኬታማ አድርጎታል- ገቢዎች ሚኒስቴር

አዲስ አበባ ፤ ህዳር 18/2016 (ኢዜአ) ፡-በቴክኖሎጂ የታገዘና አዳዲስ የክፍያ ስርአት በመተግበሩ የግብር ክፍያውን ስኬታማ ያደረገው መሆኑን የገቢዎች ሚኒስትር አይናለም ንጉሴ ገለጹ።

የ2016 በጀት ዓመት የአራት ወራት የስራ አፈፃፀም በማስመልከት የገቢዎች ሚኒስትር አይናለም ንጉሴ መግለጫ ሰጥተዋል።

በመግለጫቸውም የገቢ አሰባሰብ ስርዓቱ በቴክኖሎጂ የታገዘና ፈጣን አሰራርን የተከተለ በመሆኑ በየጊዜው እድገት እያሳየ መሆኑን ተናግረዋል።

በዚህም በበጀት አመቱ አራት ወራት 196 ቢሊዮን ብር ገቢ ለመሰብሰብ ታቅዶ ከ193 ቢሊየን ብር በላይ ማሳካት መቻሉን ጠቅሰው የተሰበሰበው ገቢ ከአምና ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር የ30 ቢሊዮን ብር ብልጫ አለው ብለዋል።

በአራት ወራት 129 ቢሊዮን ብር ከአገር ውስጥ ታክስ፤ ከ64 ቢሊዮን ብር በላይ ደግሞ ከጉምሩክ መሰብሰቡንም ሚኒስትሯ በመግለጫቸው አንስተዋል።

በአራት ወራት ከ165 ቢሊዮን ብር በላይ ለገንዘብ ሚኒስቴር ፈሰስ መደረጉን ገልጸዋል።

በሀገሪቷ አንዳንድ አካባቢዎች የተፈጠሩ የጸጥታ ችግሮች በገቢ አሰባሰቡ ሂደት ላይ ጫና ያሳደረ ቢሆንም በሚገኙት አጋጣሚዎች በቴክኖሎጂ በመታገዝ በተቀላጠፈ መልኩ መሰብሰቡን ተናግረዋል።

በሌላ በኩል የገቢና ወጪ የኮንትሮባንድ እንቅስቃሴ የታክስ አሰባሰብ ስርዓቱ ፈተና ሆኖ መቀጠሉን ሚኒስትሯ አንስተዋል።

በዚህም ባለፉት አራት ወራት ብቻ ከ4 ቢሊዮን ብር በላይ ግምታዊ ዋጋ ያላቸው የወጪና ገቢ የኮንትሮባንድ እቃዎች መያዛቸውን ገልጸዋል።

በኮንትሮባንድና ህገወጥ ደረሰኝ ግብይት ማጭበርበር 312 ግለሰቦች ተይዘው ከነዚህ መካከል 258 ተጠያቂ እንዲሆኑ ተደርጓልም ነው ያሉት።

በኤሌክትሮኒክስ ግብራቸውን በማሳወቅ ክፍያ መፈፀም የሚችሉ ግብር ከፋዮች በርካቶች መሆናቸውን ጠቅሰው በቀጣይም በተጠናከረ መልኩ ይቀጥላል ብለዋል።

በግብር ክፍያ ስርአቱ ማንኛውም ግብር ከፋይ በቴሌ ብር እና በተለያዩ የባንክ አማራጮች ባለበት ሆኖ መክፈል የሚችል በመሆኑ በዚሁ መልኩ ግደታቸውን መፈፀማቸውን እንዲቀጥሉ ሚኒስትሯ ጠይቀዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም