የአሪ ብሄረሰብ የዘመን መለወጫ በዓል ''ድሽታግና'' እየተከበረ ነው

ጂንካ፤ ህዳር 18/2016 (ኢዜአ)፦በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የሚገኙት የኣሪ ብሔረሰብ አባላት አሮጌውን አመት ሸኝተው አዲሱን አመት የሚቀበሉበት የድሽታግና በዓል በማህበረሰብ ደረጃ መከበር መጀመሩን የአሪ ዞን ቱሪዝም መምሪያ አስታውቋል።

የድሽታግና በዓል በባህል መሪዎች ቡራኬ የሚሰጥበት ታላቅ የምስጋናና የምረቃ በዓል ነው ።


 

የዞኑ ባህልና ቱሪዝም መምሪያ ኃላፊ አቶ ኤሊያስ ቃሾ ድሽታግና አብሮነትን የሚያስተምር ህዝብ ለህዝብ የሚያቀራርብ ዕሴት ያለው በዓል መሆኑን ገልጸዋል።

በዓሉ ከኣሪ ብሔረሰብ አልፎ ለመላው ኢትዮጵያዊያን የሚሆን ጠቃሚ እሴቶችን እንደያዘም ገልፀዋል።

የድሽታግና በዓል እንደ ሌሎቹ ክብረ በዓላት አድጎ፣ ጎልብቶ እንዲሁም ዕውቅና አግኝቶ ከአገራችን አልፎ የአለም ቅርስ እንዲሆን ኢትዮጵያዊያን እገዛ ሊያደርጉ ይገባል ብለዋል ።

በመምሪያው የባህል፣ ታሪክ፣ ቅርስ ጥናትና ልማት የስራ ሂደት አስተባባሪ አቶ ዳኜ ገብሬ በበኩላቸው እንደገለጹት የድሽታግና በዓል የብሔረሰቡ አባላት ፈጣሪን የሚያመሰግኑበት ነው።

አርሶ አደሩ የዘራው ዘር ፍሬ አፍርቶ ጎተራው ሲሞላ ፣ ከብቶች ተዋልደው ጋጥ ሲሞሉና ቤቱ በበረከት ሲትረፈረፍ ፈጣሪን የሚያመሰግኑበትም ነው።


 

በባህሉ መሰረት ወደ አዲሱ አመት ለመሻገር ቂምና ቁርሾን ማስወገድ የግድ እንደሆነ ገልጸው ድሽታግና በዳይም ተበዳይም ይቅር ተባብለው ቂም በቀልን በማስወገድ አዲሱን አመት በፍቅር የሚቀበሉበት ዕለት መሆኑን አስረድተዋል።

የኣሪ ብሔረሰብ አባል የሆኑት አቶ ፍቃዱ ጋሲ፥ የድሽታግና በዓል የፍቅር የአንድነትና የይቅርታ አስተምህሮ ያለው አብሮነትን የሚያጠናክር ታላቅ ክብረ በዓል በመሆኑ በየዓመቱ በጉጉት የሚጠብቁት እንደሆነ ተናግረዋል።

የዘንድሮውን የድሽታግና በአልም አብሮነትን፣ አንድነትን፣ መረዳዳትን በሚያጎላና የባህሉን እሴት በጠበቀ መልኩ ለማክበር መዘጋጀታቸውን ገልፀዋል።

ሌላዋ የብሔረሰቡ አባል ወይዘሮ ደብሪቱ ኣዳዮ ፥የድሽታግና በዓል የተጣሉትን በማስታረቅ ፣ከተቸገሩ ወገኖች ጋር ቤት ያፈራውን አብሮ በመቋደስ ፣የታመሙትን በመጠየቅ በጋራ የምናከብረው ነው ብለዋል።

ድሽታግና ፍቅር ፣አንድነት እና በጎነት ጎልቶ የሚታይበት ዕለት እንደሆነ የገለፁት ወይዘሮዋ በዓሉ በዕርቅ የማይቋጭ ጥል እና የማይሽር ጠባሳ እንደሌለ እንደሚያሳይም አስረድተዋል።


 

የኣሪ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አብረሃም አታ ፤የዘንድሮው የድሽታግና በዓል ''ድሽታግና ለዘላቂ ሰላም እና ለፈጣን ልማት''በሚል መሪ ሀሳብ በዞኑ ሁሉም አካባቢዎች በድምቀት እንደሚከበር ተናግረዋል።

በዓሉ የመተሳሰብ፣ የመረዳዳት እና የዕርቀ-ሰላም በመሆኑ የተጣላውን በማስታረቅ ፣የተቸገሩ ወገኖችን በመጎብኘትና ማዕድ በማጋራት ከአጎራባች ዞኖችና ከመላው ኢትዮጵያዊያን ጋር በጋራ ለማክበር ዝግጅት መጠናቀቁን ተናግረዋል።

ከወርሃ ህዳር አጋማሽ ጀምሮ ከቤተሰብ እስከ ኣሪ ባላባቶች ቅደም ተከተሉን ጠብቆ የሚከበረው የድሽታግና በአል ታህሳስ አንድ ቀን የዘመን መለወጫ አዲስ አመት ሆኖ በብሄረሰቡ አባላት ይበሰራል።

 

 

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም