የጎሬ_ማሻ_ቴፒ አስፋልት መንገድ ፕሮጀክት ግንባታ መጓተት ለተለያዩ ችግሮች ዳርጎናል - ነዋሪዎች - ኢዜአ አማርኛ
የጎሬ_ማሻ_ቴፒ አስፋልት መንገድ ፕሮጀክት ግንባታ መጓተት ለተለያዩ ችግሮች ዳርጎናል - ነዋሪዎች

መቱ ፤ሕዳር 18/2016 (ኢዜአ)፦ የጎሬ_ማሻ_ቴፒ አስፋልት መንገድ ፕሮጀክት ግንባታ መጓተት ለተለያዩ ችግሮች ዳርጎናል ሲሉ የአካባቢው ነዋሪዎች ቅሬታ አቀረቡ።
ኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር በበኩሉ የመንገድ ግንባታ መጓተቱን አምኖ ችግሩ የተፈጠረው በአካባቢው ባለው ረጅም የዝናብ ወራትና ከወሰን ማስከበር ጋር የተያያዘ መሆኑን ገልጿል።
ከአራት ዓመት በፊት የተጀመረው የጎሬ_ማሻ_ቴፒ አስፋልት መንገድ ግንባታ መጓተት የተለያዩ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮችን እያስከተለባቸው መሆኑን የኢሉባቦር ዞን ዲዱና ኖኖ ወረዳ ነዋሪዎች ቅሬታ አቅርበዋል።
በመንገዱ በመደበኛነት የሚጠቀሙት የዲዱና የኖኖ ወረዳ ነዋሪዎች ለኢዜአ እንደገለጹት የመንገዱ ግንባታ መጓተት ወላድ እናቶች ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ እያሳደረ መሆኑን ገልጸዋል።
የዲዱ ወረዳ ነዋሪ ፈቀደ ኦብሳ እንዳሉት መንገዱ በግንባታ ምክንያት ተነካክቶ የበለጠ በመበላሸቱ ለከፍተኛ ሕክምና ወደመቱ ሆስፒታል የሚላኩ ታማሚዎች ለችግርና አደጋ እንዲጋለጡ እያደረጋቸው መሆኑን ተናግረዋል።
መንገዱ ተገንብቶ የነበረባቸውን ችግር እንደሚፈታላቸው ተስፋ ሲያደርጉ እንደነበረ ገልጸው፤ የመንገዱ ብልሽት ለከፋ ችግር እያጋለጣቸው መሆኑን አንስተዋል።
የመንገዱ በወቅቱ ባለመጠናቀቁ አሽከርካሪዎች ከፍተኛ ታሪፍ እያስከፈሉ በመሆኑ ሕብረተሰቡ ለከፍተኛ ወጪ እንዲጋለጥ እያደረገ መሆኑን የተናገሩት ደግሞ አቶ አባተ ዳኜ ናቸው።
ከዚህም በተጨማሪ ኀብረተሰቡ የሚያመርተውን ምርት ለገበያ በማቅረብ ተጠቃሚ ለመሆን በሚያደርገው ጥረት ላይም እንቅፋት እንደሆነ ነው የገለፁት።
የመንገዱ ግንባታ መጓተት ኅብረተሰቡን ለተለያዩ ችግሮች ከማጋለጥ ባለፈ የመልካም አስተዳደር ችግር እየሆነ መምጣቱን የገለፁት ደግሞ የዲዱ ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ ሙሉጌታ አበራ ናቸው።
የኢሉባቦር ዞን ምክትል አስተዳዳሪ አቶ ጌታሁን ካሳሁን በበኩላቸው የመንገዱ ግንባታ ለረዥም ጊዜ መጓተት የዲዱና ኖኖ ወረዳዎች ላይ ከፍተኛ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮችን እያስከተለ እንደሚገኝ ገልፀዋል።
ከደቡብ ምዕራብ ክልል አዋሳኝ ወረዳዎች ጋር የሚደረገውን የንግድና ሁለንተናዊ ግንኙነቶች ላይም እንቅፋት መፍጠሩን ገልጸው፤ በአካባቢው ነዋሪዎች ዘንድ የቅሬታ ምንጭ መሆኑን አክለዋል።
በኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር የጎሬ_ማሻ_ቴፒ አስፋልት መንገድ ግንባታ ፕሮጀክት ምክትል ስራ አስኪያጅ አቶ ዘውዱ ምንውዬለት፣ የመንገዱ ግንባታ ገና 44 በመቶ ላይ ይገኛል ብለዋል።
ፕሮጀክቱ የ140 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለው ሲሆን ኦሮሚያን ከደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል የሚያገናኝ ነውም ብለዋል።
ለመጓተቱ ዋነኞቹ ምክንያቶች መካከል በአካባቢው ለረዥም ወራት የሚጥለው ከፍተኛ ዝናብ፣ የወሰን ማስከበር ችግርና ከፍተኛ የሆነ የትራፊክ ፍሰት በአከባቢው መኖሩ ነው ይላሉ።
በተጨማሪም ኮንትራክተሮች በሙሉ አቅማቸው ያለመስራትም ለመንገዱ ግንባታ መጓተት ከሚጠቀሱ ምክንያቶች እንደሆነም አብራርተዋል።
ግንባታው ከአራት ዓመት በፊት በ138 ሚሊዮን ዶላር የተጀመረ መሆኑንም አቶ ዘውዱ ገልፀዋል።
የግንባታውን መጓተት ተከትሎ 76 ኪሎ ሜትሩ ለቻይናው ሲ.አር.ሲ.ኢ.ጂ የግንባታ ድርጅት የተሰጠ ሲሆን የመንገዱ አጠቃላይ ግንባታም በቀጣዮቹ ሶስት ዓመታት ለማጠናቀቅ እንደሚሰራም ተነስቷል።