ኦስትሪያ በማዕድን፣ በታዳሽ ሃይል፣ በግብርና እና በእንስሳት እርባታ ዘርፎች ከኢትዮጵያ ጋር መተባበር እንደምትፈልግ አስታወቀች

አዲስ አበባ ፤ ህዳር 18/2016 (ኢዜአ) ፦ ኦስትሪያ በማዕድን፣ በታዳሽ ሃይል፣ በግብርና እና በእንስሳት እርባታ ዘርፎች ላይ ከኢትዮጵያ ጋር መተባበር እንደምትፈልግ አስታውቃለች።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ ከኦስትሪያ መራሄ መንግስት ልዩ ተወካይ ፒተር ላውንስኪ-ቲፈንታል ጋር ተወያይተዋል።

በውይይታቸውም ኦስትሪያ ከኢትዮጵያ ጋር በማዕድን፣ ታዳሽ ኃይል፣ ግብርና እና በሌሎች ዘርፎች ትብብር ማድረግ እንደምትፈልግ የሀገሪቱ መራሄ መንግስት ልዩ ተወካይ ፒተር ላውንስኪ-ቲፈንታል ገልጸዋል፡፡


 

ውይይቱ በሁለትዮሽ ግንኙነት፣ በኢኮኖሚያዊ እድሎች እና የጋራ ጠቀሜታ ባላቸው ቀጣናዊ ልማቶች ላይ ያተኮረ መሆኑን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ይጠቁማል።

አምባሳደር ምስጋኑ በአዲስ አበባ የሚገኘው የኦስትሪያ ኤምባሲ የሁለቱን ሀገራት የሁለትዮሽ ግንኙነት ለማስቀጠል አበረታች ሚና እንደሚጫወት ገልጸዋል።

ልዩ ተወካይ ፒተር በበኩላቸው ኦስትሪያ ከኢትዮጵያ ጋር የረጅም ጊዜ ወዳጅነት እንዳላት ገልፀው እንደ ማዕድን፣ ታዳሽ ሃይል፣ ግብርና እና የእንስሳት እርባታ ባሉ ዘርፎች ለመተባበር ፍላጎት እንደላት ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም