ለ18ኛው የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በዓል በቂ ዝግጅት ተደርጓል - አፈ ጉባኤ አገኘሁ ተሻገር - ኢዜአ አማርኛ
ለ18ኛው የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በዓል በቂ ዝግጅት ተደርጓል - አፈ ጉባኤ አገኘሁ ተሻገር
አዲስ አበባ ፤ ህዳር 18/2016 (ኢዜአ) ፡- ለ18ኛው የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በዓል በቂ ዝግጅት መደረጉን የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ አገኘሁ ተሻገር ገለጹ።
አፈ-ጉባኤ አገኘሁ ተሻገር በፌዴሬሽን ምክር ቤት አስተባባሪነትና በሶማሌ ክልላዊ መንግሥት አስተናጋጅነት ለሚከበረው 18ኛው የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በዓል በቂ ዝግጅት እንደተደረገ ተናግረዋል፡፡
በዓሉ «ብዝኃነትና እኩልነት ለሀገራዊ አንድነት» በሚል መሪ ሀሳብ በጅግጅጋ ከተማ ይከበራል፡፡
አፈ ጉባኤው በጅግጅጋ ከተማ በመገኘት ለበዓሉ እየተከናወኑ ያሉ ዝግጅቶችን ከተመለከቱ በኋላ አስተናጋጁ ሶማሌ ክልል የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች አምባሳደር የሆኑ እንግዶችን ለመቀበል በቂ ዝግጅት በማድረግ እየተጠባበቀች መሆኗን አስታውቀዋል።
በዓሉ ከመቼውም ጊዜ በላይ አንድነታችንን የምናጠናክርበትና ለሰላም ዘብ የምንቆምበት፣ ከልዩነት ይልቅ አንድነት ስር እንዲሰድ የሚሰራበት መሆኑንም ገልጸዋል።
እንዲሁም መመካከርንና መግባባትን ባህሉ የሚያደርግ፤ ጥያቄዎችን ሁሉ በፌዴራል ሥርዓቱ አግባብ በንግግርና በውይይት እንዲፈቱ የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በጋራ የሚቆሙበት ወሳኝ የታሪክ ምዕራፍ ላይ መገኘታችንን አጉልተን የምናሳይበት ነው ብለዋል።
በሶማሌ ክልል የተመለከቱት የቅድመ ዝግጅት ሥራም ይህን መሠረታዊ ነጥብ ማዕከል ያደረገ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
የሶማሌ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኢብራሂም ሁስማን በበኩላቸው ለ18ኛው የኢትዮጵያ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በዓል ሰፊ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች እንደተሠሩ ጠቁመዋል።
ክልሉን የማስተዋወቅ ሥራም በትኩረት እየተሠራ እንደሚገኝ ጠቁመዋል።