በበጀት አመቱ አራት ወራት ከ193 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ ተሰበሰበ - ኢዜአ አማርኛ
በበጀት አመቱ አራት ወራት ከ193 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ ተሰበሰበ

አዲስ አበባ ፤ ህዳር 18/2016 (ኢዜአ) ፡- በበጀት አመቱ አራት ወራት ከ193 ቢሊየን ብር በላይ ገቢ መሰብሰቡን የገቢዎች ሚኒስትር ዓይናለም ንጉሴ ገለጹ።
የ2016 በጀት ዓመት የአራት ወራት የስራ አፈፃፀምን አስመልክተው ሚኒስትሯ መግለጫ ሰጥተዋል።
በመግለጫቸውም በሀገሪቱ አንዳንድ አካባቢዎች የጸጥታ ችግሮች አጋጥመው ለገቢ አሰባሰቡ እንቅፋት ቢሆንም ኢኮኖሚው የሚያመነጨውን ገቢ የመሰብሰብ አቅም እየጎለበተ መምጣቱን ገልፀዋል።
የገቢ አሰባሰቡ እየጨመረ የመጣው ከዕቅድ ዝግጅት እስከ አሰባሰብ በልዩ ትኩረትና በቴክኖሎጂ የታገዘ ቀልጣፋ አሰራር በመዘርጋቱ መሆኑን ተናግረዋል።
በዚህም በበጀት አመቱ አራት ወራት 196 ቢሊዮን ብር ገቢ ለመሰብሰብ ታቅዶ ከ193 ቢሊየን ብር በላይ ማሳካት መቻሉን ሚኒስትሯ ገልጸዋል።
የተሰበሰበው ገቢም ከአምና ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር የ30 ቢሊዮን ብር ብልጫ እንዳለው ጠቅሰዋል።
በአራት ወራት 129 ቢሊዮን ብር ከአገር ውስጥ ታክስ፤ ከ64 ቢሊዮን ብር በላይ ደግሞ ከጉምሩክ መሰብሰቡንም ሚኒስትሯ በመግለጫቸው አንስተዋል።
በአራት ወራት ከ165 ቢሊዮን ብር በላይ ለገንዘብ ሚኒስቴር ፈሰስ መደረጉንም ገልጸዋል።
ከአራት ቢሊዮን ብር በላይ ግምታዊ ዋጋ ያላቸው የወጪና ገቢ የኮንትሮባንድ እቃዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውንም ነው ሚኒስትሯ የተናገሩት።
በህገወጥ ደረሰኝ ግብይት ማጭበርበር ሲፈፅሙ የተገኙ 312 ግለሰቦች ተይዘው ከእነዚህም መካከል 258 ተጠያቂ እንዲሆኑ ተደርጓል ነው ያሉት።