አፍሪካ በተ.መ.ድ የአየር ንብረት ጉባዔ /ኮፕ 28/ የጋራ አጀንዳዋን በአንድ ድምፅ ታሰማለች

166

አዲስ አበባ ፤ ህዳር 18/2016 (ኢዜአ) ፡- አፍሪካ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የአየር ንብረት ጉባዔ /ኮፕ 28/ የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል "አንድ ድምፅ" ታሰማለች ሲል አፍሪካ ኅብረት ገለፀ።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የአየር ንብረት ጉባዔ (ኮፕ 28) በተባበሩት አረብ ኤምሬትስ፤ በዱባይ ከነገ በስቲያ ይጀመራል።

በጉባዔው የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል የተደረሱ ስምምነቶችና ድንጋጌዎች ተግባራዊነታቸው ምን ላይ እንደደረሰ ይገመግማል።

ጎን ለጎን አገራት የአየር ንብረት ለማቋቋም በተለይም የታዳሽ ኃይል አማራጮችን በማስፋት እየተሰሩ ያሉ ሥራዎች ምክክር ይደረግባቸዋል።

ታዳጊ አገራት በአየር ንብረት ለውጥ የሚደርስባቸውን አደጋ ለመቋቋምና የኃይል ሽግግር እንዲያደርጉ የሚያስችሉ የፋይናንስ አቅርቦት ላይም ጉባዔው ትኩረት ያደርጋል ተብሏል።

በተጨማሪም የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል አገራት አዲስ የትብብር ማዕቀፍ ሊፈጥሩ እንደሚችሉም ጉባዔው ከወዲሁ ትልቅ ግምት ተሰጥቶታል።  

ጉባዔውን በማስመልከት ኢዜአ ያነጋገራቸው የአፍሪካ ሕብረት የግሪን ዎል ኢንሼቲቭ ዳይሬክተር ኢልቪስ ፖል፤ አፍሪካ አጀንዳዋን በጉባዔው በአንድ ድምፅ ታሰማለች ብለዋል።

ጉባዔው ከዚህ ቀደም በአህጉሪቱ የአየር ንብረት ለውጥ ለመቋቋም የተደረሱ ስምምነቶች ወደ ተግባር ለመቀየርና በዘርፉ የፋይናንስ አቀርቦትን ለማስፋት ዕድል እንደሚፈጥር ገልፀዋል።  

የአፍሪካ ሕብረት የግብርና፣ የገጠር ልማት፣ የብሉ ኢኮኖሚና የዘላቂ አካባቢ ኮሚሽነር አምባሳደር ጆሴፋ ሳኮ፤ አፍሪካ በጉባዔው በንቃት ትሳተፋለች ብለዋል።  


 

በተለይም በቅርቡ በኬንያ ናይሮቢ በተካሄደው የአፍሪካ ሕብረት የአየር ንብረት ጉባዔ በጋራ የተያዙ አቋሞች አፍሪካ በጉባዔው ውጤታማ ተሳትፎ እንዲኖራት መሠረት ይጥላል ብለዋል። 

ይህንንም ተከትሎ አፍሪካ በጉባዔው የአየር ንብረት ለውጥ መቋቋም ቀዳሚ አጀንዳዋ ታደርጋለች ነው ያሉት።

አፍሪካ ምንም እንኳን የበካይ ጋዝ ልቀቷ አነስተኛ ቢሆንም በአየር ንብረት ለውጥ አህጉሪቱ ድርቅ፣ ጎርፍና መሰል የተፈጥሮ አደጋዎች እያስተናገደች ትገኛለች።  

አፍሪካ በአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖ የደረሰባትን ጉዳት ለመቋቋምና ወደ ታዳሽ ኃይል ሽግግር እንድታደርግ የፋይናንስ ድጋፍ ማፈላለግ ሌላኛው አጀንዳዋ እንደሚሆን አንስተዋል።        

የዓለም ሙቀት የመጨመር ምጣኔ በአማካይ ከ1 ነጥብ 5 እስከ 2 ዲግሪ ሴሊሽየስ ለማድረግ የተደረሰው የፓሪስ ሥምምነት እውን ለማድረግ እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ2030 የዓለም የበካይ ጋዝ የልቀት ምጣኔ ከ28 እስከ 40 በመቶ መቀነስ እንዳለበት የተባበሩት መንግሥታት ደርጅት መረጃ ያሳያል።

በተባበሩት አረብ ኤምሬትስ ዱባይ ኅዳር 20 የሚጀምረው የመንግሥታቱ ድርጅት የአየር ንብረት ጉባዔ (ኮፕ 28) እስከ ታህሳስ 2 ቀን 2016 ዓ.ም ይቆያል።  

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም