በዕውቀት የበለጸገ ዜጋ ለመፍጠር በትምህርት ዘርፉ የሚደረገው የማሻሻያ ሥራ ተጠናክሮ ይቀጥላል

አዲስ አበባ ፤ ህዳር 18/2016 (ኢዜአ) ፡- በዕውቀት የበለጸገ ዜጋ ለመፍጠር በትምህርት ዘርፉ የሚደረገው የማሻሻያ ሥራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ ገለጹ።  

32ኛው የትምህርት ጉባኤ በጅግጅጋ ከተማ እየተካሄደ ይገኛል። 


 

የትምህርት ሚኒስትር ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ በዚሁ ጊዜ፤ ባለፉት ሁለት ዓመታት በትምህርት ዘርፉ የተሰራው ሥራ ያለንበትን ደረጃ ቁልጭ አድርጎ ያሳየ ነው ብለዋል።

በትምህርት ሥርዓቱ እየተደረገ ያለው ማሻሻያ ብቁ ዜጎችን ለመፍጠር ዕድል የሚሰጥ መሆኑን ገልጸው የተደረገው የማሻሻያ ሥራም ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ተናግረዋል።

የሶማሌ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ኢብራሂም ኡስማን በበኩላቸው፤ በአንድ አገር ዕድገትና የማኅበረሰብ ለውጥ ለማምጣት ብዛትና ጥራት ያለው የተማረ ዜጋ ወሳኝ ነው።


 

ትምህርት ቤቶች ዕውቀት የሚሹ፣ በክህሎት የዳበሩና በሥነ-ምግባር የታነጹ ዜጎችን ለማፍራት ትኩረት ማድረግ እንዳለባቸው ተናግረዋል።

በኢትዮጵያ ባለፉት ዓመታት የትምህርት ተቋማትን ከማስፋፋት አንጻር ሰፊ ሥራ መሰራቱን ጠቁመው ጥራትን ለማረጋገጥ ግን አሁንም ብዙ መሰራት ይጠይቃል ብለዋል። 

አሁን ላይ መንግሥት በትምህርት ሥርዓቱ ላይ ያለውን ስብራት ለመጠገን ዘርፈ ብዙ ሥራዎችን በመሥራት ላይ እንደሚገኝም ተናግረዋል።

ለዚህም አዲስ የትምህርት ፖሊሲ በመቅረጽ ከታችኛው የትምህርት እርከን ጀምሮ ጥራትን ለማረጋገጥ የሚያስችሉ በርካታ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን አስረድተዋል።

በሶማሌ ክልልም የተከሰቱ የተፈጥሮ አደጋዎችን በመቋቋም የትምህርት ተቋማትን በማስፋፋትና ጥራትን በማረጋገጥ አበረታች ሥራ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

ለአብነትም በሶማሌ ክልል ከሚገኙ 2 ሺ 370 የአንደኛ እና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች መካከል 573 የሚሆኑት ከለውጡ ወዲህ የተገነቡ ናቸው ብለዋል።

በክልሉ 11 አዳዲስ የአዳሪ ትምህርት ቤቶች መገንባቸውንም ጠቁመው ትምህርት ብልጽግናን ለማረጋገጥ ሁነኛ መሳሪያ መሆኑንም ነው የተናገሩት።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም