በጋምቤላ ክልል ሰላምን ይበልጥ ለማጠናከር በሚደረገው ጥረት የህዝቡ ሁለንተናዊ ተሳትፎና ድጋፍ ሊጠናከር ይገባል -ኮሚሽኑ

112

ጋምቤላ፤  ህዳር 18/2016 (ኢዜአ)፡-  በጋምቤላ ክልል ያለውን ሰላም ይበልጥ ለማጠናከር በሚደረገው ጥረት የህዝቡ ሁለንተናዊ ተሳትፎና ድጋፍ ሊጠናከር እንደሚገባ የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን አስታወቀ።

ኮሚሽኑ የክልሉን ወቅታዊ ጉዳይ በማስመልከት ዛሬ ለጋዜጠኞች መግለጫ ሰጥቷል።  

የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ኮማንደር ኡማን ኡጋላ በመግለጫቸው እንዳሉት በክልሉ ዘላቂ  ሰላም በማስፈን የተጀመሩ የልማትና የመልካም አስተዳደር ስራዎች ስኬታማ እንዲሆኑ እየተሰራ ነው።

በክልሉ እየተከናወኑ ባሉት የሰላም ግንባታ ስራዎች ቀደም ሲል የነበሩት የጸጥታ ችግሮች ተወግደው አሁን ላይ የተረጋጋ ሰላም ማስፈን መቻሉን ተናግረዋል።   

ይሁን እንጂ አንዳንድ ማህበራዊ ሚዲያዎች ሐሰተኛ መረጃዎችን በማሰራጨት የክልሉን ህዝብ ሰላም ለማወክ እየተንቀሳቀሱ እንደሚገኙ ኮሚሽነሩ ገልጸዋል።

"በተለይም ሰሞኑን በክልሉ ያልተፈጸመን ድርጊት እንደተፈጸመ በማስመሰል በማህበራዊ ሚዲያ ያሰራጩት ሀሰተኛ መረጃ የእኩይ ድርጊታቸው አብይ ማሳያ ነው" ብለዋል።

የክልሉን ሰላም በማይፈልጉ አካላት እየተሰራጨ ባለው ሐሰተኛ መረጃ ህዝቡ ሳይወናበድ ለአካባቢው ዘላቂ ሰላም ዘብ ሊቆም እንደሚገባ ኮሚሽነሩ አስገንዝበዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም